
የተፈጥሮ አካባቢዎቹ አስፈላጊው እንክብካቤ ተደርጎላቸው የታለመላቸውን ጥቅም ሊሰጡ ይገባልም ተብሏል፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 22/2012ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ለቱሪዝም፣ ለታሪክ፣ ለሳይንሳዊ ምርምር፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለተለያዩ ዓላማዎች አገልግሎት የሚውልና መጠበቅ ያለበት ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንዳለ ይነገራል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብቻ በፓርክነት እና በማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራነት እንደተከለለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ወቅቱ 1988 ዓ.ም ‹‹የአፍሪካ ጣሪያ›› በመባል የሚታወቀው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግሥታት የባህል ትምህርት እና ሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው አካባቢዎች አንዱ ሆኖ ተመዝግቦ ነበር፡፡ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ከአደጋ ለመታደግ እና በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የፓርኮችን ቁጥር ለመጨመር ሲባል ነበር የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን በአዋጅ የተቋቋመው፡፡
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን በ2008 ዓ.ም ከተጋረጠበት አደጋ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ባለስልጣኑ በ15 ዓመታት ውስጥ ወደ ብሔራዊ ፓርክ እና የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎች የሚገቡ 19 ቦታዎችን ለማጥናት አቅዶ የ16 ቦታዎችን ጥናት አሳካ፡፡ ከ16ቱ የተጠኑ አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ ወደ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ የሚገቡ 12 ቦታዎች ሕጋዊ ሰውነትን አግኝተዋል ተብሏል፡፡ ዛሬ ላይ በአማራ ክልል የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ስድስት ብሔራዊ ፓርኮች እና ሰባት የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎች አሉ፡፡
በክልሉ ከሚገኘው እና መጠበቅ ከሚገባው አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ሕጋዊ ሰውነት ያገኘው ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ እንደማይበልጥ የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ባለስልጣን የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አብርሃም ማርየ በተለይም ለአብመድ ገልፀዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ሕጋዊ ሰውነት ካገኙት ጥብቅ ስፍራዎች መካከል እንኳን በርካቶቹ በግንዛቤ እጥረት ምክንያት በሚፈለገው መጠን ወደ ሥራ አልተገባባቸውም፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ሥራ በግለሰቦች ጥረት ብቻ የሚመጣ ተግባር አለመሆኑን ያነሱት አቶ አብርሃም በተለይም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ዕውቅናና ግንዛቤ በመፍጠር የወረዳ እና ዞን ባለድርሻ አካላት የበለጠ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ ማሳያ የጉና እና ጮቄ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎች ለጣና ሐይቅ እና ለዓባይ ወንዝ ኅልውና መሠረት ቢሆኑም በአካባቢው ማኅበረሰብ ተገቢ ያልሆነ ስጋት ምክንያት የሚፈለገውን ርቀት መጓዝ አልተቻለም ተብሏል፡፡
ከጮቄ እስከ ጉና፣ ከአቡነ ዮሴፍ እስከ አልጣሽ፣ ከቦረና ሳይንት ወረ ኢመኑ እስከ መንዝ ጓሳ፣ ከባኩሳ እስከ ወለቃ በቶና ዓባይ፣ ከጎደቤ እስከ ማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም፣ ከጣና ሐይቅ እስከ ባሕር ዳር ጥቁር ዓባይ እና በክልሉ 17 ከፍተኛ ደኖች ተለይተው ሕጋዊ ሰውነት ቢሰጣቸውም አብዛኞቹ በሚፈለገው ልክ እየተጠበቁ አይደለም ነው የተባለው፡፡
‹‹የተፈጥሮ ሀብት በሰው ልጅ ቁጥር መጨመር፣ ፍላጎትና የአጠቃቀም ጫና ምክንያት ጉዳት እየደረሰባቸው ነው›› ብለዋል አቶ አብርሃም፡፡ ሥነ ምኅዳራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ኅልውናን የመታደግ ጉዳይ በመሆኑ በማኅበረሰቡ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባልም ተብሏል፡፡ኅብረተሰቡ የሀብቱ ባለቤት፣ ኃላፊ እና አስተዳዳሪ በመሆኑ በየደረጃው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የወጡት ሕጎችን፣ ዓለማቀፋዊ ስምምነቶችን የማክበር፣ የዱር እንስሳትን የመኖር መብት ማክበር፣ ለቀጣዩ ትውልድ የተፈጥሮ ሀብቱን የማስረከብ ጉዳይ በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ‹‹ሕግ ይዘን ሕግን ማስፈፀም ግን አልቻልንም›› ያሉት አቶ አብርሃም መንግሥት፣ የየአካባቢዎቹ ማኅበረሰብ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት የጋራ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው