በአማራ ክልል ከነሐሴ 23/2015 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች ምዝገባ እንደሚካሄድ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

75

ባሕር ዳር: ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2016 የትምህርት ዘመን 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ብሏል ቢሮው፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን የሀገርን እድገት ለማረጋገጥ ትምህርት ወሳኙ ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን በተሟላ ሥራ ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቢሮ ሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ እቅዶችን አውርዶ ሲሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

በሰላም መደፍረሱ ምክንያት በክልል ደረጃ የሚካሄደውን የትምህርት የንቅናቄ መድረክ እስካሁን አለማድረጋቸውንም ነዉ የገለጹት፡፡ ወቅቱ የትምህርት ንቅናቄ የሚካሄድበት መኾኑን ያነሱት ኀላፊው የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት ስለ ትምህርት የሚወያዩበትና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን የሚሠሩበት ነውም ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የተማሪዎች ምዝገባ ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም እንደሚጀምርም አስታውቀዋል፡፡ ምዝገባው እስከ ጳጉሜ 3/2015 ዓ.ም እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

ነሐሴ 23 ተማሪዎች ምዝገባ የሚጀምሩት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መኾናቸውን የተናገሩት ኀላፊው የግል ትምህርት ቤቶች ምዝገባቸውን ቀደም ብለው መጀመራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ምዝገባቸውን በማጠናቀቅ ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከነሐሴ 23 እስከ ጳጉሜ 3 ድረስ በሚቆየው የተማሪዎች ምዝገባ አዲስ ገቢ ተማሪዎች እንደሚጠበቁም አመላክተዋል፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ወደ ትምህርት ቤት እንደሚመጡም ይጠበቃል፡፡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት መማር የሚገባቸው ሕጻናትም እንዲመዘገቡ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

ከአዳዲስ ተማሪዎች በተጨማሪ ነባር ተማሪዎች፣ በተለያየ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ እና በተለያየ ምክንያት የደገሙ ተማሪዎች በሚኖሩት የምዝገባ ቀናት ይመዘገባሉም ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በመመዝገቢያ ቀናቱ መመዝገብ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል፡፡

መስከረም 2/2016 ዓ.ም ትምህርት ቤቶች እንደሚከፈቱ ያመላከቱት ኀላፊው መምህራን ትምህርት ቤት የሚገኙበት፣ ርእሰ መምህራን መማር ማስተማር የሚጀምርበትን ቀን ዝግጁ የሚያደርጉበት ሥራ እንደሚጀምርም አመላክተዋል፡፡

ከመስከረም 2 እስከ መስከረም 6 /2016 ዓ.ም በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሚጀምሩ የትምህርት አይነቶች ትውውቅ ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡ ለአብነት ግብረ ገብና የሥራና ተግባር የትምህርት አይነቶች እንደ አዲስ እንደሚሰጡም አመላክተዋል፡፡

ከመስከረም 7 እስከ 11/2016 ዓ.ም ደግሞ የትምህርት ሳምንት ተብሎ እንደሚከበር ነው የተናገሩት፡፡ የትምህርት ሳምንት ተብሎ በሚከበረው ሳምንት በ2016 ዓ.ም ስለሚኖረው ግብ ውይይት ይደረጋል ነው የተባለው፡፡

መስከረም 14/2016 ዓ.ም የዓመቱ የመማር ማስተማር ሥራው የሚጀምርበት መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ የመማር ማስተማር ሥራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጀምር ሁሉም በየድርሻው መሥራት ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

ባለፈው ዓመት የመጽሐፍ እጥረት እንደነበር ያነሱት ኀላፊው ዘንድሮ የአንደኛ ደረጃ እና የመካከለኛ ደረጃ መጽሐፍ እጥረት እንደማይገጥምም ገልጸዋል፡፡ የታተሙ መጽሐፍት ሥርጭት እየተካሄደ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ መጽሐፍቱ ወደ ትምህርት ቤቶቹ እንዲደርሱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ አሁን ላይ የሰላም ኹኔታው መሻሻል እያሳየ በመኾኑ ክልል አቀፍ የትምህርት ንቅናቄ መድረክ እንደሚኖርም አንስተዋል፡፡ በየደረጃው ያሉ የትምህርት ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ መሥራት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡ ለመማር ማስተማሩ የሚደረጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በቀሪ ጊዜያትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል፡፡

በአማራ ክልል 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች መመዝገብ አለባቸው ተብሎ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በዕቅድ የተያዙ ተማሪዎች እንዲመዘገቡ እና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማኅበረሰቡ እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ በትኩረት መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡

ትምህርት የተወዳደሪነት እና የሕልውና ጉዳይ መኾኑ መታወቅ ይገበዋል ነው ያሉት ኅላፊው፡፡ ክልሉ በትምህርት ወደ ኋላ እንዳይቀር ሁሉም መረባረብ አለበት ብለዋል፡፡ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበው በሁሉም አካባቢዎች ትምህርት እንዲሰጥ ርብርብ ማድረግ አለብን ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበ2016 ዓ.ም የላቀ ግንኙነት ለመመስረት በትኩረት እንደሚሠራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next article“ትምህርት ቤቶችን ለመገንባትና የመማር ማስተማር ሥራውን በተሟላ መንገድ ለመምራት ሰላም አስፈላጊ ነው” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ