
አዲስ አበባ: ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ባለፈው ዓመት ወዳጅነትን መመለስ ላይ በትኩረት ሲሠራ አንደነበር አንስተው በዚህም አቋም የያዙ አካላት ጋር የማለዘብ እና የማስገንዘብ ሥራ በመሥራት ወዳጂነትን የመመለስ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስረድተዋል።
አምባሳደር መለስ በ2016 ዓ.ም ይህንን ግንኙነት በማጠናከር የላቀ ጥብቅ ግንኙነትን መመስረት ላይ በትኩረት ለመሥራት እቅድ ተይዞ ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል። ይህም ኢትዮጵያ የተሻለ ብሔራዊ ጥቅሟን ያስከበረ የውጭ ግንኙነት ግብ ያለው መኾኑን አንሰተዋል።
ይህንንም ለማድረግ በዋናነት ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት በመስጠት ግንኙነትን ማጠናከር ሲኾን ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ደግሞ በዋናነት በንግድ እና በሠራተኛ ስምሪት አተኮሮ ይሠራል ተብሏል።
ከአሜሪካ ጋር የሚኖረውን ግንኙነትን በማጠናከር ንግድን በማሳደግ እና አግዋን መልሶ ለመቀላቀል ይሠራል ያሉ ሲኾን ከእስያ እና ከላቲን አሜሪካ፣ ከፓስፊክ ሀገራት ጋር እና ከአውሮፓ ሀገራት ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ይሠራል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያን በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት እና በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረሙ ስምምነቶች ኢትዮጵያ በባህረሰላጤው እና መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት እየሠራች ያለችው ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ እየከፈተች ለመኾኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መኾኗ ካላት የባለብዙ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ታሪክ ጋር የሚያያዝ እና ይህንን ለማጠናከር ብቻ ዓላማ ያለው መኾኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ ይህንን ግንኙነት ጎራ ከመለየት እና ሌላ ግንኙነትን ለመተው ዓላማ የሌለው መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!