
ባሕር ዳር: ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሞኑን በተከሰተው አለመረጋጋት እና ሁከት ነባር የማኅበረሰብ እሴቶች መሸርሸራቸውን ያሳየ ክስተት እንደነበር የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፎክለር እና የባሕል ጥናት ትምህርት ክፍል ተጠሪ ዐቢይ አስማማው (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡ ሰዎች በሃይማኖት ፣ በትምህርት እና በባሕል ያገኟቸው እና ሊጠብቋቸው የሚገቡ እሴቶች ስለመኖራቸው መምህሩ አስረድተዋል፡፡
ዶክተር አስማማው ማኅበረሰቡ ከመንግሥት በሕግ እና በመመሪያ የወረደለት፣ በሃይማኖት የተሠበከው እና በትምህርት የተማረ በመኾኑ የሚያውቃቸው እና የሚጠብቃቸው እሴቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ መንግሥታዊ እና ሃይማኖታዊ ከኾነው ሕግ ባለፈ ማኅበረሰቡ የሚጠቀምባቸው ባሕላዊ እሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ በስፋት መኖራቸውን መምህሩ ያነሳሉ፡፡ እነዚህ እሴቶች ስህተት የኾነውን ስህተት ካልኾነው፣ ደጉን ከመጥፎ፣ የሚገባውን ከማይገባው የምንለይባቸው አብረውን የኖሩ እና ከአባቶቻችን የተረከብናቸው፣ ለልጆቻችን የምናስተላልፋቸው እንደኾኑም ዶክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ እሴቶች ሰሞኑን በነበረው ግርግር እና አለመረጋጋት ወቅት መሸርሸራቸው እንደታየ ተናግረዋል፡፡ ነጋዴው ነጋዴ ከሚባልበት ማንነቱ፣ ሸማቹም ሸማች ከሚባልበት ሰውነቱ ወጥተው በማይገባቸው ቦታ ላይ ተሰልፈው እንደነበር ይናገራሉ፡፡
አንዳንድ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ያልተገባ ወሬን በማናፈስ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የተደረገው የስግብግብነት ባሕሪ ያልተገባ አካሄድ እንደኾነ እና ለእሴቶቻችን መሸርሸር ማሳያ ስለመኾናቸው አስገንዝበዋል፡፡ ነጋዴው ማኅበረሰቡ የራሱ ወገን መኾኑን እያወቀ፣ ነገ ሕልውናው የተመሰረተው በማኅበረሰቡ ላይ መኾኑን ዘንግቶ፣ ዛሬ ብቻ ልብላ በሚል ያሳየው ያልተለመደ ተግባር በርካታ ሰዎችን ለጉዳት አጋልጧል ይላሉ፡፡ መግዛት የሚችል በተጠየቀው ዋጋ ሲሸምት፣ መግዛት የማይችለውን ዜጋ በያዘው እና ለእርሱ ባልኾነ ወይም በብዝበዛ ባመጣው ገንዘብ ሸማቹን ያሸማቀቀበት ኹኔታ ያልተለመደ እና ከእሴቶቻችን ለመውጣታችን ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡ መንግሥትም ቢኾን እንደነዚህ አይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባ እንደነበረ አንስተዋል፡፡
የነጋዴው መኖር በማኅበረሰቡ ኅልውና ላይ የተመሠረተ ቢኾንም አንዳንድ ነጋዴዎች እኔ ብቻ ልብላ በማለታቸው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አድርገው ሕዝቡን ሲያሰቃዩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ምስቅልቅሎሽ ሲፈጠር ከዚህ ለመውጣት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡
ሃይማኖታዊ የኾነው አስተምህሮና ባሕላዊ የኾኑ እሴቶቻችን ለኑሮአችን አጋዥ ሊኾኑ እንደሚገባም ያነሳሉ፡፡
ማንኛውም ሰው የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ቢኾን የእምነቱን አስተምህሮ ማወቅ ብቻ ሳይኾን በሕይወት ኑሮ ሊተገብረው ይገባል እንጂ ማወቅ ብቻውን ዋጋ አይኖረውም ነው ያሉት፡፡ አብሮነት ፣መተሳሰብ ፣መረዳዳት እና መተጋጋዝ እንዲሁም የሰዎችን ችግር መረዳት አብረው የሚያኖሩን እሴቶቻችን ናቸው የሚሉት መምህሩ ማኅበረሰቡ እነዚህን ጠብቆ ማቆየት ለሌሎች ማስተላለፍ እና ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ዶክተር ዐቢይ እንዳሉት ከምስቅልቅሎሽ ለመውጣት ለእሴቶቻችን ዋጋ መሥጠት በእነሱንም መመራት ተገቢ ነው፡፡ እሴቶቻችን ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ከመንግሥት በተጨማሪ የሃይማኖት አባቶች፣ የእቁብ፣ የእድር እና ሌሎች ማኅበራዊ ተቋማት አጥብቀው ሊሠሩ ይገባል፤ በተጨማሪ ሁሉም የራሱን ኀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ መምህሩ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!