
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ለ2016 ዓ.ም የትምሕርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን አስታውቋል። የባለፈውን ትምሕርት ዘመን ጥንካሬና ውስንነት በመለየት በክረምቱ ልዩ ልዩ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውንም መምሪያው አመላክቷል። በዚህም መሰረት የነባር ትምህርት ቤቶች እድሳት፣ አዳዲስ የትምህርት መሰረተ ልማቶችን የመሥራትና የትምሕርት ቁሳቁስን የማሟላት ሥራ ተሠርተዋል ነው የተባለው። በ2015 ዓ.ም የነበረው የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት መቀረፉም ተመላክቷል።
የመምሪያው ኀላፊ ጥበቡ ገሰሱ እንዳሉት በተያዘው ክረምት 20 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ተጠናቅቀው ለሥራ ዝግጁ ሆነዋል። በከተማ አስተዳደሩ በሁሉም የትምህርት ደረጃ 79 የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን በ2016 የትምህርት ዘመን 55 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ መታቀዱንም አቶ ጥበቡ ገልጸዋል። ከነሐሴ 23/2015 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች ምዝገባ እንደሚካሄድም መምሪያው አስታውቋል።
ዘጋቢ:–ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!