
ባሕር ዳር: ነሐሴ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከከተማዋ ነዋሪ ሴቶች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ላይ ውይይት አድርጓል።
የመምሪያው ኀላፊ ወይዘሮ የሻረግ ፈንታሁን እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ አስራቴ ሙጨ በሚያወያዩበት ወቅት ሰላም እና ግጭት በተከሰተ ጊዜ ሴቶች እና ሕጻናት ቅድሚያ ተጎጅዎች ናቸው ብለዋል። በክልሉ ብሎም በሀገር የተሟላ ሰላም እንዲሰፍን ሴቶች ስለሰላም ገንቢ ውይይትና ምክክር ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት። እንደ ሕዝብ ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲሰጣቸው የሰከነ ትግል ማድረግ እንጅ የዜጎችን ሕይወት ወደሚቀጥፍ ግጭት መገባት የለበትም ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
“ኢትዮጵያዊያን እናቶች በጥበባቸው ግጭቶችን ማርገብ ይችላሉ” ያሉት መምሪያ ኀላፊዋ ግጭት እና መገዳደልን ማውገዝ እና ወጣቶች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ማስከን እንዳለባቸው መልእክት አስተላልፈዋል። የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዋ ወይዘሮ አስራቴ ሙጨ በበኩላቸው ወጣቶች ከግጭት እንዲርቁ እና ለሰላም ብቻ እንዲቆሙ የእናቶች፣ የእህቶች እና የሚስቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
“በተፈጠረው ግጭት ሕይወታቸውን እያጡ የሚገኙት ሁሉም የእኛው ልጆች ናቸው” ያሉት ወይዘሮ አስራቴ ግጭቶችን በማስወገድ ሰላማዊ ክልል እና ሀገር መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ሴቶች በሙሉ አቅማቸው ለሰላም ከሠሩ በአጭር ጊዜ የሚፈለገውን ሰላም ማምጣት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
በተወያዮች ከተነሱ ሃሳቦች መካከልም:-
✍️ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች በአስቸኳይ መፍታት ከቻለ ልጆቻችንን እና ባሎቻችንን ለሰላም መክረን ለማስከን ቀላል ይሆንልናል ብለዋል።
✍️በተፈጠረው ግጭት እና አለመረጋጋት በተለይም በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ከፍተኛ ጫና እያስከተለ መኾኑን መንግሥት ተረድቶ ሰላማዊ ውይይቶች በአስቸኳይ ይጀመሩ።
✍️ በግጭት ምክንያት የተባባሰው የኑሮ ውድነት በተለይም ሴቶችን በከፍተኛ ኹኔታ እየፈተነ ነው።
✍️ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የጸጥታ አካላት ሕዝብን የሚያረጋጉ ተግባራትን በትኩረት መሥራት አለባቸው። ከዚህ ተቃራኒ የኾኑ እና ሕዝብን ወደ ቁጣ የሚገፉ ንግግሮች እና ድርጊቶችን መንግሥት መቆጣጠር እና በአስቸኳይ ማረም አለበት።
✍️ የአማራ ክልል ሴቶች ለኢትዮጵያ ሲሉ የሚዋደቁ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ችግር በገጠማቸው ጊዜ አንገታቸውን ቀና አድርገው አጉርሰዋል፤ ልብሳቸውን አጥበው ቀይረዋል፤ ለሀገር ዘብ እንዲኾኑም መርቀው በመላክ ደጀንነታቸውን አሳይተዋል። ይህ ውለታ በሠራዊት አባላት ጭምር የማይረሳ ቢኾንም መከላከያን ከአማራ ክልል ሕዝብ ለማቃረን የሚደረግ አሉባልታ መቆም አለበት።
✍️ሀገር ሰላም እንድትኾን መንግሥት ሴቶችን በማወያየት ሃሳብ እና ጥበባቸውን መጠቀም አለበት።
✍️ አማራ ክልል የሕዝቡን ስሜት እና ፍላጎት እያጠና የሚረዳ እና በየጊዜው የማይቀያየር አመራር ያስፈልገዋል።
✍️ ሴቶች በስሜታዊነት የሚንቀሳቀሱ ወጣት ልጆቻቸውን፣ ባሎቻቸውን እና ወንድሞቻቸውን በመምከር እና በማስከን ለሀገር ሰላም መትጋት አለባቸው።
✍️ መሳሪያ የሀገር ዳር ድንበር መጠበቂያ መኾን ሲገባው በየሰፈሩ እየተተኮሰ፤ ሴቶች እና ሕጻናትን ለሥነ ልቦና ችግር እያጋለጠ እና የሰዎችንም ሕይወት እየቀጠፈ በመኾኑ ሕገ ወጥ ተኩስ በሕግ የተከለከለ እና ቁጥጥር የሚደረግበት መኾን አለበት፡፡
✍️ ወጣት ልጆች አልባሌ የግጭት ቦታ ሲውሉ እናቶች ቀርበው መጠየቅ እና ማስተካከል አለባቸው።
✍️ ወጣቶችን ወደ ስሜታዊነት የሚገፋፉ የወሰን እና ማንነት እንዲሁም የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መመለስ መቻል አለባቸው። በመንግሥት በኩል መልስ ለመስጠት ያስቸገሩ ጥያቄዎች ሲገጥሙም በግልጽ መወያየት ያስፈልጋል።
✍️ ግጭቶች ሲከሰቱ ሕይወት ከመጥፋቱ እና ንብረት ከመውደሙ በፊት አስቸኳይ ውይይት እና ምክክር የማድረግ ባሕል እንደመንግሥት እና ሕዝብ መዳበር አለበት፡፡
✍️ የሀገር እና የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን እና ንብረትን የሚያወድሙ ወጣቶችን በጋራ ማውገዝ እና በሕግ እንዲጠየቁ መሥራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!