
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 21/2012ዓ.ም (አብመድ) አሁን ባለው እሳቤ አዝማሪ ድምፃዊ እና የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችና ድምጻዊ ነው፡፡ ቀደም ባለው እሳቤ ደግሞ አዝማሪ አመሥጋኝ፤ የሃይማኖታዊ ዝማሬዎች መሪ ነበር፡፡ እስከ ቅርብ ዘመናት ድረስም ‹አዝማሪ› እና ‹ዓለም አጫዋች› በሚል ለሁለት ተከፍለው ቆይተዋል፡፡ አዝማሪ የሚባሉት ሃይማኖታዊ ምሥጋናን የሚያቀርቡት ሲሆኑ ዓለም አጫዋች የሚባሉት ደግሞ ዓለማዊ ዝማሬዎችን የሚያቀርቡትን ነው፡፡
አዝማሪን ባልዘመነ አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው የሚመለከቱ ሰዎች ሙያ መሆኑን ረስተው ለስድብ አገልግሎት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፤ ባሕላዊ እሴቶቻቸውን በሚያከብሩ ማኅበረሰቦች ደግሞ ሀብት ነው፡፡ አዝማሪን በዘመነኛ አጠራር ‹አርቲስት› ይሉታል፡፡ አዝማሪ ድምፃዊ እና የማሲንቆ መሳሪያ ተጫዎችም ነው፡፡ አዝማሪ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች እና አሠራሮች መሞረጃ ሆኖ ረጅም ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
ጥንታዊው የአዝማሪዎች እሴት ዛሬ ላይ እንደሀብት ሳይሆን እንደማውገዣ ሁኗል፡፡ እየመነመነ የመጣውን ይህን ዘርፍ በጠንካራ ምጣኔ ሀብት እንዲዋቀር እና ታሪካዊ እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ ሠላም ኢትዮጵያ የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ከደብረ ታቦርና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ምክክር አድርጓል፡፡ አብመድ ከአዝማሪዎች እና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
የኮራሁ አዝማሪዎች ማኅበር ሰብሳቤ ወረታው ማለደ ‹‹ልጄ አዝማሪነቴን ያፍርበታል፡፡ በትምህርት ቤት ‹የአባትህ ሥራ ምንድን ነው?› ተብሎ ሲጠየቅ ‹ሹፌር ነው› ብሏቸዋል፡፡ ለምን እንደዋሸ ስጠይቀው ‹የአዝማሪ ልጅ› እያሉ እንዳይሰድቡኝ ነው›› አለኝ፤ በዚህም ‹‹አዘንኩ ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ የኖርኩበት ሙያ ነው፤ እኔ አዝማሪ ነኝ፡፡ አዝማሪነቴ የምተዳደርበት እንጀራየ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ከሐዘናቸው እንዲወጡ የማበረታታ፤ ደስታቸውን የማደምቅ ከያኔ ነኝ፡፡ ዛሬን አሳያለሁ፤ ዛሬን አመሳጥሬም ነገን የምተነብይ አዝማሪ ነኝ፡፡ ግን ድምጽ አልባዎች ነን፡፡ ደስታቸውን ስላደመቅኩ፣ ከሐዘናቸውም ስላወጣሁ፤ ነገንም ስለተነበይኩ ስሜን ‹አዝማሪ› እያሉ ያሳነሱ ይመስላቸዋል፡፡ ይኼ ነገር ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ አዝማሪነት የአንገት መድፊያ ሙያ ሁኗል፡፡ ልጀቻችን እያፈሩብን፤ ሰዎች እያሸማቀቁን አዝማሪነት በዚህ ዘመን እየተመናመነ የመጣ ሙያ ሁኗል›› ነው ያሉት ሊቀ መኳስ ወረታው ማለደ፡፡
የአዝማሪነትን ሙያ ሕዝቡ ማራቁና ማሳነሱ ሙያተኞችም በኢኮኖሚ እንዲጎዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ አዝማሪነት እንደጥበቡ ዘላቂ የመተዳደሪያ ኢኮኖሚ መፍጠር ባለመቻሉ ሙያው ተዳክሟል፤ አዳዲስ ግጥሞችን መስማት ሲቻል ተደጋጋሚ ግጥሞች ይሰማሉ፣ ሙያው የስብሰባ ማድመቂያ እና የእንግዳ ተቀባይና ሸኝ ሁኖ ይታያል፤ በዚህም ባለሙያዎቹ ያዝናሉ፡፡ “እኔም የልጄን ክብር ከፍ ለማድረግ በቅርቡ ሹፌር ሁኛለሁ” ብለዋል ሊቀ መኳስ ወረታው ማለደ፡፡
ሊቀ መኳስ ወረታው ማለደ ቀደም ብሎ ‹‹አዝማሪ ምን አለ? ምን ይናገር ይሆን ተብሎ ይጠበቅ ነበር? አሁን ግን በየሠርግ ቤቱ፣ በየምሽት ቤቱ ‹አታደንቁሩኝ› የሚለው በዝቷል›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ዘርፉ እንዲያድግ ሕዝቡ አዝማሪነት ጥበብ እንጂ የልመና ሙያ እንዳልሆነ በአመለካከት ሊቀየር እንደሚገባና መንግሥትም ዘርፉን በተቋም ደረጃ ማምጣትና ማሳደግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የቴአትርና የፈልም ጥበባት መምህር አስናቀው ዓለሙ የአዝማሪዎችን አቅም ለመዝናኛ እና ለኢኮኖሚ ምንጭነት ለመጠቀም መገናኛ ብዙኃን ጉልህ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃን ኪነ ጥበብን ለዘገባ ማሳመሪያ ሳይሆን ለማኅበረሰብ ጥቅም እንዲውሉ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ የአዝማሪ ሙያ ማኅበራትን በማቋቋም በባህል ፖሊሲ አማካኝነት ለጥበብ የሚበጀተው በጀት መንግሥት በትክክል ለሀገር በቀል ሙያዎች ሊያውለው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ኢብራሂም ዳምጠው ‹‹በነገሥታቱ ዘመን አዝማሪነት ተቋም ነበር፡፡ በእስልምና መንዙማ በኢትዮጵያዊ ቅኝት የተቃኘ ልዩ ሥራ መሆን የቻለው በአዝማሪዎች ፈናወጊነት ነው›› ብለዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴአትርና የፊልም ጥበባት መምህር ምሥጋናው ዓለሙ ‹‹በኢትዮጵያ አዝማሪነት ትናንት እና ዛሬ›› በሚል መነሻ ጥናታቸው አዝማሪዎች ምስጢርን መግለጽ ብቻ ሳይሆን ነገን እንደሚተነብዩ አመላክተዋል፡፡
አዝማሪነት በመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ እንደተመላከተው ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የማኅበረሰብ ማረቂያ፣ የነገሥታት ውሎን በግጥሞች ለትውልድ ማስተላለፍያ ሙያ እንደነበር ተጽፏል። በኢትዮጵያም አዝማሪዎች በንግሥተ ሳባ ዘመን እንደተጀመረ መረጃዎች እንዳሉ ያመላከቱት መምህር ምሥጋናው ‹‹በዘመናቱ ጎንጦ የማያቆስል፣ ማኅበራዊ ሒስ ማስኬጃ ሁኖ ኖሯል›› ብለዋል፡፡
‹‹የአዝማሪነት ሙያ እየተመናመነ የመጣው የፈጠራ ችሎታቸው በማነሱ እና ተተኪ ትውልድ ባለመፍጠራቸው ነው፡፡ ተተኪ ትውልድ ያልተፈጠረው ደግሞ አዝማሪነት እንደሙያ ሳይሆን እንደልመና በመታየቱ ነው›› ብለዋል፡፡ መንግሥት ባሕልን ወደ ቱሪዝም ገበያ ለማሳደግ እንደተቋም ማደራጀት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡ የአዝማሪዎችን ክብር ለማሳደግ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የአመለካከት ለውጥ፣ ትምህርትና ስልጠና እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶክተር) ‹‹አዝማሪ ጥበብን በቀላሉ ከእነለዛው የሚያስተምር የቆየ ባህላዊ ሀብት ነው›› ብለዋል፡፡ አዝማሪዎች በሀገሪቱ ሠላም ለማረጋገጥና ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ሚና ስላላቸው ዩኒቨርሲቲው ዕድገቱ ትኩረት ሠጥቶ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንድሪስ አብዱ የክልሉ መንግሥት ዘርፉን ለማጠናከር እስከ ወረዳ የሚተገበር እቅድ አውጥቶ እየሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አዝማሪዎች ዛሬን በግጥም ለነገ ትውልድ ያሻግራሉ፡፡ ጀግንነትን በማሳበቅ፣ ክፋትን በማረቅ የሕዝቦችን እርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከር የሚችሉ ‹ድምጽ አልባ› ባለውለታዎች ናቸው፡፡ ለሰዎች ክብር መስጠት ሰብዓዊ ነው፤ አዝማሪዎች እንዲከበሩ ማድረግ ባሕላዊ እሴቶች እንዲጠናከሩ ያደርጋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ