የተካረረ የጽንፍ አመለካከት ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ብሔራዊ እርቅ ሳያካሂዱ ወደ ምርጫ መግባት ተገቢ አለመሆኑን ዛሬ ጥምረት የፈጠሩ ፓርቲዎች አሳሰቡ፡፡

306

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 21/2012ዓ.ም (አብመድ) ‹‹የኢትዮጵያ ኮንፌዴራሊስት ኃይሎች በሀገሪቱ ኅልውና ላይ ሊፈጥሩት የሚችሉትን አደጋ ለመቋቋም አልመናል›› በሚል ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ፈጠሩ፡፡

ጥምረቱም ‹አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮት)› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፤ ጥምረቱን የፈጠሩት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) እና ኅብር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ጥምረቱም እውነተኛ ፌዴራሊዝምን በመፍጠር ጎራ ያጣውን የፖለቲካ አስተሳሰብ ለማስተካከል እንደሆነ የፓለቲካ ፓርቲዎቹ አሳውቀዋል፡፡

ይህ ጥምረት ‹‹የ2012 ዓ.ም ሀገር ዓቀፍ ምርጫ መካሄድ የለበትም›› የሚል አቋም አለው፡፡ እንደ አብሮነት አቋም የተካረረ የጽንፍ አመለካከት ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ብሔራዊ እርቅ ሳያካሂዱ ወደ ምርጫ መግባት የተጀመረውን ለውጥ ተስፋ አስቆራጭ ብቻ ሳይሆን የመክሸፍ አደጋ እንደገጠመው ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

ጥምረቱ ‹ኮንፌዴራሊስት ኃይል› ሲል የገለፃቸው በኦሮሚያ ዙሪያ የተሰባሰቡ እና ሰሞኑን በትግራይ ክልል ‹‹ፌዴራላዊ ሥርዓትን እንታደግ›› በሚል ሲሰባሰቡ የነበሩ ኃይሎች መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡ እውነተኛ ፌዴራሊዝም መመሥረት የሚፈልጉ ኃይሎች ግን ወደፊት ወደ አብሮነት እንዲቀላቀሉ ጥምረቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

Previous article‹‹‹ሽፍታ እየቀለባችሁ ስለሆነ ልትጠየቁ ነው› ብለው ነው የወሰዱን፡፡›› ከዕገታ ያመለጠው ታዳጊ
Next articleአዝማሪዎች ሀገራዊ ችግሮችን ነቅሰው እያወጡ በመተቸት እንዲስተካከሉ የማድረግ የቀድሞ አቅማቸውን ለምን አጡ?