ከቀናት በፊት ግጭት እና አለመረጋጋት የነበረባት የአማኑኤል ከተማ ሰላሟ መመለሱን ነዋሪዎች ተናገሩ።

96

ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሚገኘው የማቻከል ወረዳ ዋና ከተማ የኾነችው አማኑኤል ከተማ ከግጭት እና አለመረጋጋት ሙሉ በሙሉ ወጥታ ሰላሟ መመለሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከተማዋ ከነሐሴ 14/2015 ዓ.ም ጀምሮ በሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ስለመኾኗ ነው ነዋሪዎቹ የተነገሩት።

ከዚህ ቀን ጀምሮ መጠነኛ የባጃጅ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ስለመጀመሩ የገለጹት ነዋሪዎች አሁን ላይ መደበኛ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል። ለሳምንታት የተዘጋው የከተማዋ እንቅስቃሴ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጫና ፈጥሮ መቆየቱንም ነዋሪዎች ጠቅሰዋል።

✍️ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ሱቆች እና ሌሎችም የንግድ ቤቶች ተከፍተው ሥራ ጀምረዋል።
✍️ካፌዎች እና ምግብ ቤቶችም የተለመደ አገልግሎታቸውን እየሰጡ ነው።
✍️አሁን ላይ በከተማዋ የጸጥታ ስጋት እንደሌለም ነዋሪዎች ለአሚኮ ተናግረዋል።

የተገኘውን ሰላም ዘላቂ እንዲኾን ሁሉም ነዋሪዎች በትብብር መሥራት እንዳለባቸውም ነዋሪዎቹ አሳስበዋል። በአካባቢው የሚገኙና የሚመለከታቸው የኮማንድ ፖስቱ አመራሮች ወደ ሕዝቡ ወርደው ውይይት እንዲያደርጉ ነዋሪዎች የጠየቁ ሲኾን የተገኘውን ሰላም ማዝለቅ እንደሚያስፈልግም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አሁን ላይ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር ባይኖርም ባንኮች ግን እንዳልተከፈቱ ነው የጠቆሙት። እንደሌሎች የንግድ ተቋማት ባንኮችም ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአማራ ክልል ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ማኅበረሰቡ ተቋማትን ከከፋ ዘረፋና ውድመት ታድጓል” የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን
Next articleኢትዮጵያ በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴቶች 1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ አገኘች።