
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በየምክንያቱ ለሚፈጠሩ ችግሮች ማኅበረሰቡን የሰላሙ ጠባቂ በማድረግ በኩል የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት (ኮሙኒቲ ፖሊሲንግ) ሚና የጎላ እንደኾነ ነው የክልሉ ፖሊስ የገለጸው፡፡
በ1995 ዓ.ም በክልል ደረጃ በሞዴል የተጀመረው የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊሰ አገልግሎት ማኅበረሰቡ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት መሥራትን፣ በየአካባቢው የሰላሙና የደኅንነቱ ጠባቂ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ውጤት እየታየበት ስለመኾኑ ነው የተነገረው፡፡
በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በአለፉት ሳምንታት ከነበረው ወቅታዊ አለመረጋጋትና ግጭት ወጥቶ ወደ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት እየተመለሰ ነው ብሏል ፖሊስ፡፡
በተለይ የሰላምና ጸጥታ ችግር ገጥሞ በነበረበት ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው ችግር የበለጠ ጉዳት፣ ውድመትና ዝርፊያ እንዳያደርስ ኅብረተሰቡ የፖሊስነት ተግባርን ሲፈጽም ቆይቷል ብሏል፡፡
በዋናነት የወንጀል መከላከል ሥራውን ከማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽንሰ ሃሳብ በመነሳት ኅብረተሰቡ በራሱ ፖሊስ ኾኖ ታይቷል፡፡ ፖሊስ ጣቢያን ጨምሮ ሌሎችም ተቋማት በተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት ከዘረፋና ውድመት መታደግ እንደተቻለም ተገልጿል።
በርካታ ተቋማት በማኅበረሰቡ ተጠብቀዋል ፤ ይህም የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ውጤት እንደኾነ ነው የተገለጸው፡፡ በክልሉ በተፈጠረው አለመረጋጋትና ግጭት ማኅበረሰቡ ተቋማትን ከከፋ ዘረፋና ውድመት ታድጓል ብሏል የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፡፡
እንደችግሩ አፈጣጠርና እንደ ችግሩ ስፋት የከፋ ጉዳት ይደርስ ነበር፤ ነገር ግን በኅብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረው ጠንካራ እሴት ፣ ማኅበረሰቡ እራሱ የሰላሙ ጠባቂ በመኾን ጥፋቱን እንደቀነሰው ነው የተገለጸው፡፡
ይህ መልካም እሴት ችግሩ ያልተፈጠረባቸው አካባቢዎችም ከሌሎች በመረዳት ቀድሞ የመምከር፤ ቀድሞ የመሥራት ኹኔታ እየታየ ነው ፣ ችግር ሲፈጠር የዜጎችን ደኅንነትና የሃብት ንብረት ውድመትን ለመታደግ የሚያስችል አደረጃጀትም እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ፖሊስ መረጃ ማኅበረሰቡ በአካባቢው ችግር እንዳይፈጠር አቅም የመኾን ፣ ለተፈጠረው ችግርም ወደ ሰላም እንዲመለስ የነበረው ተሳትፎ አበረታች ነው ተብሏል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለአሚኮ በሰጠው መረጃ ባሕር ዳር ከተማና አካባቢውን ጭምሮ ሌሎችም ወደ ቀደመ ሰላማቸው የተመለሱ አካባቢዎች የተዘረፉ የግለሰብና የተቋማትን ንብረቶች የመመለስ ሥራም ተጀምሯል፡፡
ከአቅም በላይ ኾኖ የተፈጠረን ችግር ተነጋግሮ የማረም ፤ የተዘረፈን ሃብትና ንብረት ማስመለስ ፤ ጉዳት የደረሰበትን መልሶ የማደስ ሥራ እየታየ እንደኾነም ነው የተገለጸው፡፡
የአማራ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ፤ በሕግና ሥርዓት የመመራት ባሕሉ የዳበረ ነውና እንደኹኔታው የሚፈጠሩ ተደጋጋሚ ችግሮችን በሰከነ መልኩ በመፍታት የሚታወቅ ነው የሚለው የፖሊስ መረጃ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትም አቅም በመኾን አገልግሏል ብሏል፡፡
በቀጣይም ማኅበረሰቡ በጎ ልምዶችን በማስቀጠል የሰላሙ ዘብ ፤ የሃብት ንብረቶችም ጠባቂ በመኾን የክልሉን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ በኩል ሚናውን እንዲወጣም አሳስቧል፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!