“ኮረም ከሰቆጣ አንድ ነው እትብቱ ሳየው ደስ ይለኛል ዋግሹም ያለበቱ”

55

ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደግነት መለኪያ፣ የጀግና መፍለቂያ፣ የሩህሩዎች መኖሪያ፣ የሀገር ወዳዶች መናኸሪያ፡፡ ሀገራቸውን አብዝተው ይወዳሉ፤ ለሠንደቅ ሲሉ ከፊት ቀድመው ይወድቃሉ። ለሀገር ክብር ሲሉ ደማቸውን ያፈስሳሉ፤ አጥንታቸውን ይከሰክሳሉ፤ ሀገራቸውን የሚነካባቸውን አብዝተው ይጠላሉ፡፡ ለሚወዱት ይሞቱለታል፣ እነርሱ ተርበው ያጎርሱታል፣ አንተ ኑር እኛ እንሙት ይሉታል፡፡

ከራስ በላይ ለሰዎች ይኖራሉ፣ በፍቅራቸውና በደግነታቸው ሠንሰለት የሰውን ልብ አስረው ይኖራሉ፣ እነርሱ የተራበን ማጉረስ፣ የታረዘን ማልበስ ይችሉበታል፡፡ ባሕል አክባሪዎች፣ ሃይማኖት ጠባቂዎች፣ ሀገር አፍቃሪዎች፣ ጀግናና ኩሩዎች ናቸው፡፡

በዚያ ምድር ኢትዮጵያ ላቅ ያለችበት፣ ጥንታዊነቷ፣ ኀያልነቷ፣ ታላቅነቷ፣ የጥበብ አምባነቷ፣ የጀግና ማሕጸንነቷ የሚገለጽበት ሞልቷል፡፡ ብልኾች፣ ጀግኖች፣ ሩህሩሆች እና ልበ ቀናዎች እየተነሱ ስለ ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ ሠርተውበታል፣ ኢትዮጵያንም ከፍ አድርገው አስጠርተውባታል፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ታላቅ ነገር ይሠራባታል፡፡

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን አብዝተው ይወዳሉ፣ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ ይሰጣሉ፣ ባሕልና ሃይማኖትን አብዝተው ይጠብቃሉ፣ ያስጠብቃሉ፣ ሳይበረዝና ሳይከለስ ለልጅ ልጅ ያስተላልፋሉ ዋግሹሞች የዋግኸምራ ጀግኖች፡፡ በዚያ ምድር ባሕልና ወግ ሥርዓቱን ጠብቆ ዛሬ ድረስ ደርሷል፡፡

እነሆ ነሐሴ ላይ እንገኛለን፡፡ ወንዞች ባዘቶ መስለዋል፣ ተራራዎች፣ ሸለቆዎች፣ ኮረብታዎች እና ሜዳዎች በአረንጓዴ ካባ ተሸፍነዋል፡፡ ሰዎች ሁሉ የክረምቱን ቡቃያ በአዲሱ ዓመት አፍርቶ ለማየት ጓጉተዋል፡፡ እንዲህ ታላቅ ተስፋ በሚሰነቅበት፣ የክረምቱ ማብቃት እየታሰበ አዲስ ዓመት በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት በዋግሹሞች ምድር ሻደይ ይከበራል፡፡

ሻደይ እኒያ መልከ መልካም ወይዛዝርት ጥሩ ለብሰው፣ ጥሩ በልተው፣ ጥሩ ጠጥተው ሰላምና ፍቅርን ይሰብኩበታል፡፡ ጎበዛዝቱም ያማረ ቁምጣቸውን ለብሰው፣ ጎፈሬያቸውን አሳምረው፣ ቂቤ የጠገበች በትራቸውን ይዘው፣ እንዲያም ሲል መውዜራቸውን አንግተው ደምቀው የሚታዩበት በዓል ነው፡፡
ይህ የሻደይ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓል ለዘመናት ሲከበር ኖሯል፡፡ ዛሬም እየተከበረ ነው፡፡ የዋግሹም ልጆች በቀያቸውና በአድባራቸው ሻደይን እያከበሩት በየአድባራቱ እጅ እየነሱ ለምድር ሰላም እጅ እየነሱበት ነው፡፡

ለዓመታት ከማንነታቸው እና ከባሕላቸው ተነጥለው የቆዩት የወፍላና የኮረም ነዋሪዎችም ሻደይን በድምቀት እያከበሩት ነው፡፡ ወፍላና ኮረም በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በባሕል፣ በወግና ሥርዓት፣ በመልካዓ ምድር ከዋግ ጋር አንድ የነበረ፣ አንድ ኾኖ የኖረ ነው፡፡
“ ኮረም ከሰቆጣ አንድ ነው እትብቱ

ሳየው ደስ ይለኛል ዋግሹም ያለበቱ” እንደተባለ ኮረምና ሰቆጣ ማንነቱ አንድ የኾነ፣ ከፍ ያለ ታሪክ የተሠራበት፣ የሀገር ፍቅር የረቀቀበት ነው፡፡ የዋግሹሞች ታሪክ ሲነሳ ኮረምና ወፍላ ከጠቅላላው ከዋግ ምድር ጋር አብረው ይነሳሉ፡፡ አብረውም ይወሳሉ፡፡

የዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ መሳይ ጸጋው ሻደይ በዋግኸምራ በሁሉም አካባቢዎች የሚከበር ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓል መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ሻደይ ዘንድሮም እንደ ወትሮው ሁሉ በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሁሉም ወረዳዎች እየተከበረ መኾኑን ገልጸዋል ኀላፊው፡፡ በተለየ ኹኔታ ደግሞ በኮረም በቅርብ ርቀት በሚገኘው አሸንጌ ሐይቅ እየተከበረ ነው ብለዋል፡፡ በአሸንጌ እየተከበረ የሚገኘው የሻደይ በዓል እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚከበር ደማቅ በዓል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የኮረምና የወፍላ አካባቢዎች በአለፉት ዓመታት ከዋግኸምራ ተነጥለው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ለበርካታ ዓመታትም ባሕላቸውና ማንነታቸው ተጽዕኖ ሲደርስበት ቆይቷል፡፡ ከዓመታት በኋላ ግን ወደ ትክክለኛ ማንነታቸው እና ታሪካቸው ተመልሰው የሻደይን በዓልን በአንድነት እያከበሩት ነው፡፡

በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት ከሀገር ወስጥና ከውጭ የሚመጡ እንግዶች እንዳይገኙ ቢያደርገውም በሁሉም አካባቢዎች ሕዝባዊነቱን ጠብቆ፣ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቱን አክብሮ እየተከበረ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ የሻደይ በዓል በክፉውም በደጉም ዘመን ለዘመናት እየተከበረ የኖረ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ሻደይ መሠረቱ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በመኾኑ ሕዝባዊነቱን ሳይለቅ ይከበራል ነው ያሉት፡፡ ዘንድሮም ሕዝባዊነቱ ጎልቶ እየተከበረ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡

ሃይማኖታዊና ባሕላዊ መሠረት ያለው በዓል በችግር ውስጥም ቢኾን መከበሩን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ በዓሉ የሰላም ነው ያሉት ኀላፊው ከጥንት ጀምሮ ሰላም፣ ፍቅር፣ መቻቻል የሚሰበክበት፣ በረከትና ረድኤት ከፈጣሪ ዘንድ የሚጠየቅበት፣ አሁንም ልጃገረዶች ሰላም ለምድራቸው፣ ፍቅር ለሀገራቸው ይሰጥ ዘንድ ፈጣሪያቸውን እንደሚጠይቁበትና እየጠየቁበት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

በየአድባራቱ እና በዓሉ በሚከበርባቸው ሁሉ ሰላምና ፍቅር እንደሚሰበክበትም ተናግረዋል፡፡ የወፍላና የኮረም አካባቢዎች ለዘመናት በቆየው የዋግሹሞች ሥርዓት ከዋግ ጋር አንድ ናቸው ያሉት ኀላፊው ከዓመታት በኋላ በአንድነት በማክበራቸው ስሜቱ ልዩ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ አንድ ታሪክ፣ አንድ ባሕል፣ አንድ ሥነልቦና ያለው ሕዝብ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

ለዓመታት ተለያይተው ቢቆዩም ዛሬ ግን በአንድነት እያከበሩት ነው፣ ለበዓሉም የተለየ ድባብ ሰጥቶታል ነው ያሉት፡፡ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲከበር እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቅና በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

በዓሉ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ይዘቱን ሳይለቅ ሕዝባዊ ኾኖ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት፡፡ የሕዝብ በዓላት ታሪክ፣ ሃይማኖት እና ባሕል የሚገለጽባቸው መልእክታቸው ሰላም የኾኑ ናቸውም ብለዋል፡፡ ሰላም ምን ያክል አስፈላጊ እንደኾነ ከጥንት ጀምሮ ሲሰበክባቸው እና ሲዘመርባቸው የቆዩ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ስለ ሰላም እየሰበኩ፣ ስለ ሰላም በሰላም እየተከበረ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአንሸንድዬን በላስታ፤ ሶለልን በራያ
Next article“በአማራ ክልል ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ማኅበረሰቡ ተቋማትን ከከፋ ዘረፋና ውድመት ታድጓል” የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን