
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዘወልድ፣ የመዛርድ፣ የክፍሎ እና የስንየሰገድ የአንድ ወንድም ልጆች፣ ደጋጎቹና ኩሩዎች፣ ጀግናና ልበ ቀናዎች፣ ለፍቅር ሟቾች፣ ባሕልና ወግ አክባሪዎች ራያዎች ባሕላዊና ሃይማኖታዊ በዓላቸውን በአንድነት እያከበሩ ነው፡፡
ወተትና ማር ጠጥተው ያደጉ ጀግኖች ያሉበት፣ ደጋጎችና ልበ ቀናዎች የሚኖሩበት፣ ባሕልና ሥርዓት የሚከበርበት፣ የአባትና የእናት ወግ የሚጠበቅበት ራያ ተዝቆ የማያልቅ ታሪክ፣ ባሕልና ሃይማኖት አለው፡፡ ነጭና ጥቁር ይበቅልበታል፣ ከተወደዱ ላሞች እንደ አላውኃ፣ እንደ ጎሊና ወንዞች ወተት ይቀዳበታል፣ ምድሩም ውብ ነው እሸት ይታፈስበታል፡፡
ጎበዛዝቱ መውዜራቸውን በትክሻቸው፣ ጀበርናቸውን በወገባቸው፣ በባሕላዊ ልብሳቸው ደምቀው ሲታዩ ልብን ይሰርቃሉ፡፡ ባሕላቸውን አክባሪዎች፣ ወግና ሥርዓታቸውን ጠባቂዎች ናቸውና ከዓመት እስከ ዓመት ድግና ጎፊያቸውን ለብሰው፣ በረዶ የሚመስለውን ጥርሳቸውን አንጥተው፣ ከልባቸው ላይ ታጥቀው በጀግንነት ይኖራሉ፡፡
ወይዛዝርቱ ሹርባቸውን ተሠርተው፣ በአርቲና ናትራ ተውበው፣ ያማረውን ቀሚስ በአማረው ገላቸው ላይ ደርበው፣ በቀጭን ወገባቸውም መቀነታቸውን ሸብ አድርገው ከቤት ሲወጡ አጀብ ያሰኛሉ፡፡ ውበትና ደም ግባት ለእነርሱ ተሰጥታለች፣ ማማርና መዋብ በእነርሱ ታምራለች፡፡
በየዓመቱ ነሐሴ ሲመጣ ደግሞ የወሎ ሰማይ ሥር ከውበት ላይ ውበት ትደርባለች፡፡ እኒያ ተፈጥሮ ውብ አድርጎ የሠራቸው ወይዛዝርት እና ጎበዛዝት ሀገር ባበቀለው፤ ተፈጥሮ ባደለው መዋቢያ ተውበው ይወጣሉ፡፡ ሶለል እና አሸንድዬ እያሉ ከቀያቸው ምድርን ያደምቃሉ፡፡ ለአምላካቸውም ምሥጋናና ውዳሴ ያቀርባሉ፤ ከአበው እና ከእመው ፊት እጅ እየነሱ ምርቃት ይቀበላሉ፡፡ ከዓመት እስከ ዓመት ኖረው ይገናኙ ዘንድ ይመኛሉ፡፡ ባሕልና ወጋቸውን ሃይማኖትና ታሪካቸውን ይጠብቃሉ፡፡
እነሆ ወረኃ ነሐሴ ደርሷል፡፡ አሸንድዬና ሶለል እየተከበሩ ነው፡፡ ወይዛዝርቱና ጎበዛዝቱም አምረው ወጥተዋል፡፡ በዓላቱም ደምቀዋል፡፡
የሰሜን ወሎ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ፀሐይነው ሲሳይ በሰሜን ወሎ ዞን የአሸንድዬና ሶለል በዓላት በሰሜን ወሎ እየተከበሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ የአሸንድዬ እና ሶለል በዓላት ባለፈው ዓመት በድምቀት መከበራቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ የኾነው በዓል በሰሜን ወሎ ዞን በራያ አላማጣ ሶለል፣ በላስታ ላሊበላ አሸንድዬ እየተከበሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ሲፈጸም ማደሩንም ተናግረዋል፡፡ በላሊበላ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ዛሬም ሲከበር እንደሚውል ነው የገለጹት፡፡ ለባሕሉና ለታሪኩ ሟች በኾነው ራያ ዞናዊ መልክ ይዞ በራያ አላማጣ በድምቀት እየተከበረ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ በራያ አላማጣ እየተከበረ ያለው በዓል ደማቅ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው በራያ አላማጣ በዓሉ ትናንት በፓናል ውይይት መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡
ራያዎች በአንድነት፣ በነጻነት እና በፍቅር በዓላቸውን እያከበሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የዘንድሮ በዓል ለራያ ልዩ ትርጉም ያለው መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ራያ ለታሪኩ፣ ለማንነቱ፣ ለነጻነቱ፣ ለባሕሉና ለወግ ሥርዓቱ ሲታገል ኖሮ በአንድነት እያከበረ ነውና፡፡ ከአንድ ወንዝ የሚቀዱት፣ አንድ ባሕል ያላቸው ራያዎች በፖለቲካ ሽፍጥ ተከፋፍለው መኖራቸው ይታወሳል፡፡ በዓሉ “ባሕላችን ለሰላም ለአንድነት እና ለማንነታችን” በሚል መሪ ሳብ እየተከበረ መኾኑንም ገልጸዋል። ባሕል ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለማንነት ትልቅ ፋይዳ አለው ያሉት ኀላፊው በዓላቱ የአካባቢውን ትክከለኛ ማንነት በማሳየት በኩል ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ ነውም ብለዋል፡፡
የራያ ሕዝብ በማንነቱ ምክንያት ተጽዕኖ ሲደርስበት የኖረ ሕዝብ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በዓሉን በነጻነት እንዳያከበር ጫና ሲደረግበት እና ባሕሉን እና ታሪኩን ሲሻሙት እንደኖሩም ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ላይ ባገኘው ሰላም እና ነጻነት ወግና ሥርዓቱን ጠብቆ ባሕሉን በነጻነት እያሳየ ነውም ብለዋል፡፡ የራያ ሕዝብ በአንድነት በራሱ ፍላጎትና ተነሳሽነት እያከበረ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ባሕሉ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ይዘቱ ሳይቀየር ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የወልድያ ዩኒቨርሲቲም ጥናትና ምርምር በማድረግ እገዛ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ትክክለኛውን የአመጋገብ፣ አለባበስ፣ አጨፋፈር እና አጠቃላይ ሥነ ሥርዓት ወግና ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲቆይ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ ባሕሉን መጠበቅ ማንነትን እና ታሪክን ለትወልድ ከማስተላለፍ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም ላቅ ያለ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ጌጥ የኾኑት በዓላት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገቡ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ዛሬ ላይ አላማጣ ላይ በፍጹም ሰላም እየተከበረ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የራያን ባሕል የራስ አድርጎ ለመውሰድ የሚደረጉ ሙከራዎች አግባብ አለመኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሶለል እና አሸንድዬን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ጠብቆ የማቆየት ሥራው ተጠናክሮ ይቆያልም ብለዋል፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ከራያ እስከ ቅዱስ ላሊበላ ድረስ ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች ያሉት ዞን መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የራያና የላስታ በአጠቃላይ የሰሜን ወሎ ሕዝብ ለማንነቱ እና ለታሪኩ ወደኋላ የማይል ሕዝብ ነው ያሉት ኀላፊው ሕዝቡ ባሕሉን እንዲጠብቅ የማድረግ ሥራ እየሠራን ነውም ብለዋል፡፡
የራያ ሕዝብ በጋራ በዓሉን እያከበረ፣ ታሪኩን እየዘከረ፣ ባሕሉን እያሳመረ መኾኑንም ነግረውናል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!