
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር መንገድ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ሳሙኤል ወርቅነህ እንዳሉት በባሕርዳር በተከሰተው የሰላም እጦት በከተማዋ ይሠሩ የነበሩ ትላልቅ የአስፓልት መንገዶች ፣ የሪዳክሽን መንገዶች፣ የዲሽ ቦይ፣ ክሮሲንግ ስላም ፣ የመብራት ዝርጋታ እና መሰል የልማት ሥራዎች መቆማቸውን ተናግረዋል፡፡
ከሰላም እጦት ጋር በተገናኘ ሠራተኞችን እና የሥራውን ትላልቅ ባለሙያዎች ማግኘት እና ሥራውን ማስቀጠል አስቸጋሪ እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡
ከተማ አሥተዳደሩ አጋጥሞት በነበረው የሰላም እጦት የመንገድ ማሽኖችን ለማስቀመጥ እና ሥራውን ለማስቀጠል አስቸጋሪ ኾኖ መቆየቱን አብራርተዋል፡፡
የሰላም እጦቱ የመንገድ ሥራዎችን ከማቆም ባለፈ በመንገድ ሥራዎች ላይ የደረሱ ጥፋቶችም መኖራቸውን ነው ያስረዱት፡፡
በተለይ ከዚህ በፊት ከፍተኛ ወጭ ወጥቶባቸው በተሠሩ መንገዶች ላይ ጎማ በማቃጠል ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስባቸው ስለመደረጉም ምክትል ሥራ አሥኪያጁ ነግረውናል፡፡
መንገዶቹ በሕዝብ ከሚሰበሰብ ገንዘብ የሚሠሩ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ከመኾናቸው ባለፈ መንገዶቹን በቀላሉ ለመጠገን አስቸጋሪ በመኾኑ ጉዳቱን የከፋ እንደሚያደርገውም ነው ያስገነዘቡት፡፡
መንገዶች የትኛውም አካል ቢመጣ የሚገለገልበት ሕዝብ በመኾኑ እና ጠቀሜታውም ለሕዝብ በመኾኑ ጥፋት እንዳይደርስ በማድረግ በኩል ሕዝቡ የበኩሉን ድርሻ መወጣት መቻል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
መንገዶቹ የሚገነቡት በውጭ ተቋራጮች በመኾኑ በሰላም እጦት ምክንያት የመንገዶች የግንባታ ሥራ ሲዘገይ ተጨማሪ ገንዘብ ስለሚጠይቁ እንደ ሀገርም ኾነ እንደክልል ብዙ ኪሳራ እንደሚያስከትል መገንዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የግንባታ እቃ በተለይም በአስፓልት ሥራ የጥሬ እቃ በየጊዜው የሚጨምር በመኾኑ በሕዝብ ላይ የሚያደርሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ በቀላሉ የሚታይ አለመኾኑንም ነው ያስረዱት፡፡
እንደ ግለሰብም ኾነ እንደማኅበረሰብ ለመልማት እና ተጠቃሚ ለመኾን ሰላም አስፈላጊ በመኾኑ ቆም ብሎ እና ሰክኖ ማሰብ እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡
በተለይም ማኅበረሰቡ ማኅበራዊ መሰረተ ልማቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እና ሥራቸውም እንዳይስተጓጎል አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግና ሰላሙንም እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ።- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!