
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ በተለያ አካባቢዎች ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች ዋጋቸው አሻቅቦ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
በመደበኛው ወቅት ከ55 ብር እስከ 75 ብር ይሸጥ የነበረው ቀይ ሽንኩርት በአለመረጋጋቱ ወቅት ከ140 ብር እስከ 150 ብር እንደተሸጠ አሚኮ በነበረው ቅኝት ተመልክቷል፡፡ አሁን ግን ዋጋው ወደ 80 ብር መውረድ ችሏል፡፡
✍️በሰላሙ ወቅት ከ730 እስከ 880 ብር በሊትር ይሸጥ የነበረው የተለያየ አይነት ዘይት በችግሩ ወቅት ከ1 ሺህ 100 እስከ 1ሺህ 400 ብር ተሸጧል፣ አሁን በተገኘው ሰላም ከ930 እስከ 1ሺህ 100 ብር እየተሸጠ ነው፡፡
✍️ከ25 ብር እስከ 30 ብር ለኪሎ ይሸጥ የነበረው ድንች በችግሩ ወቅት ከ80 እስከ 90 ብር ተሸጧል፣ አሁን በመጣው ሰላም ደግሞ ከ25 እስከ 30 ብር እየተሸጠ ነው፡፡
✍️ከ30 ብር እስከ 40 ብር በኪሎ ይሸጥ የነበረው ቲማቲም በችግሩ ወቅት ከ110 እስከ 120 ብር ተሸጧል፣ አሁን ላይም እስከ ከ100 ብር እየተሸጠ ነው፡፡
✍️90 ብር ይሸጥ የነበረ መኮረኒ ከ130 እስከ 140 ብር ተሽጦ የነበረ ሲኾን ፤ አሁን ላይ ደግሞ 110 ብር እየተሸጠ ነው፡፡
✍️ከ55 ብር እስከ 60 ብር ይሸጥ የነበረው ፓስታ በችግሩ ወቅት 70 ብር ተሸጧል፤ አሁን በመጣው ሰላም 60 ብር እየተሸጠ ነው፡፡
✍️እስካሁን ምንም ጭማሪ ያላሳዬው ምስር ክክ ሲኾን አሁንም በነበረበት ዋጋ 170 ብር እየተሸጠ መኾኑን አሚኮ ተመልክቷል፡፡
አሚኮ ባደረገው ቅኝት ከነሐሴ 8 እስከ 10 /2015 ዓ.ም ላይ ይታዩ ከነበረው ወከባ እና አለመረጋጋት ወጥቶ ሻጭም ገዥም በተረጋጋ መንፈስ ሲገበያዩ ተመልክቷል፡፡
“የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል” እንደሚባለው የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተገን አድርጎ የሸማቹን ኪስ ለማራቆት የተዘጋጁ በሚመስሉ ስግብግብ ነጋዴዎች እንደተነዛው ወሬ ሳይኾን ቀርቶ ሰው ወደ መደበኛ የግብይት ሂደቱ መመለሱን አሚኮ ባደረገው የገበያ ቅኝት መታዘብ ችሏል፡፡
የተገኘውን ሰላም የበለጠ ዘላቂ በማድረግ እና ምርትን ከቦታ ወደ ቦታ በበቂ ሁኔታ በማንቀሳቀስ ሸቀጦቹ አሁንም እየተሸጡ ካሉበት ዋጋ የበለጠ ይቀንሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!