በላሊበላ ከተማ የተገኘውን ሰላም የበለጠ በማጽናት ጎብኝዎች በነጻነት ወደከተማዋ እንዲመጡ እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ ።

52

ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ንጉሥ ወ ቅዱስ ላሊበላ ውብ አድርጎ ያነጻት፣ የዓለምን ጥበብ ሽሮ አዲስ ጥበብ ለዓለም ያሳየባት፣ ዓለትን እንደ ግራምጣ የሰነጠቀባት፣ ከላይ ወደታች የረቀቁ አብያተ ክርስቲያናትን የቀረጻባት፣ በቅዱስ መጽሐፍ ያለውን በምድር ያሳየባት፣ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ትኾን ዘንድ ያሳመራት፣ በቅድስና ጀምሮ በቅድስና የፈጸማት፣ በቅድስና ትኖር ዘንድ ሕግጋትን ያስቀመጠባት፣ ቅድስና ያልተለያት ውብ ምድር፡፡

በዚያች ምድር ሥርዓተ መንግሥትንና ሥርዓተ ቤተ ክህነትን አስተባብሮ ኖሮባታል፣ ኢትዮጵያን በጥበቡና በብልሃቱ አገልግሎባታል፣ ዘውድ ጭኖ በትረ መንግሥት ጨብጦ፣ በአስፈሪ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ንጉሥ ኾኖ ነግሶባታል፣ እየጾመ፣ እየጸለየ፣ እየሰገደ፣ እየቆረበ አምላክን እያመሰገነ እንደ ካህንም አገልግሎባታል፣ ላሊበላ በቤተ መንግሥት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ንጉሥ ነው፣ በቤተ ክህነት ቅድስናን የተቸረው ቅዱስ ነው፣ ጥበብ ለእርሱ ተሰጥታለች፣ መወደድ ለእርሱ ተበርክታለች፡፡ የተወደደችው ምድርም የተወደደውን ንጉሥ ወ ቅዱስ አሻራ ይዛ ኖራለች፡፡

በዚያች ምድር ቅድስና እና ንግሥና፣ ምድራዊ እና ሰማያዊ ዓለማት ወሰን ሳይተላለፉ በልካቸውና በወሰናቸው ኖረውበታል፡፡ የረቀቁ የጥበብ አሻራዎች ከትመውበታል፣ ያልተፈቱ ምስጢራት ሞልተውበታል፡፡ ጀምበር ወጥታ በጠለቀች ቁጥር አዲስ ነገር ይታይበታል፡፡ ሰርክ አዲስ ሰርክ ረቂቅ ነው፡፡

በዓለሙ ሁሉ ትናፈቃለች፣ ትወደዳለች፣ ሰዎች ሁሉ ያዩዋት ዘንድ ይመኟታል፣ ባዩዋትም ጊዜ አብዝተው ደስ ይሰኙባታል ቅድስቲቷ ከተማ ላሊበላ፡፡ ደጋጎች፣ እንግዳ ተቀባዮች፣ ብልኾች እና ጠቢቦች ይኖሩባታል፡፡ እንግዳ በሰላም ያርፍባታል፣ በደስታና በፍቅርም ይኖርባታል፤ የቀደመው ባሕልና ወግ ያልተበረዘባት፣ ወግና ሥርዓት የሚከበርባት፣ ሃይማኖት የጸናባት፣ የአበው ቃል የሚሰማማባት፣ ቃል ኪዳን የሚጠበቅባት ውብ ከተማ ናት ላሊበላ፡፡ ነዋሪዎቹ እንግዶቻቸውን እግራቸውን እያጠቡ ይቀበሏቸዋል፣ ስሞት አፈር ስኾን እያሉ ያጎርሷቸዋል፣ የተጠሙትንም ያጠጧቸዋል፣ በተመቸው ስፍራም ያሳድሯቸዋል፤ በፍቅርና በደስታ ይንከባከቧቸዋል፡፡

በዚህች ከተማ ብዙዎች ይሰባሰቡባታል፣ ታሪኳን እና በውስጧ የያዘቻቸውን እጹብ የሚያሰኙ አብያተ ክርስቲያናትን እያዩ እጹብ ድንቅ እያሉ ይገረሙባታል፡፡ ይህች የተዋበች እና የተወደደች ከተማ በውስጧ ያየዘቻቸውን የተደነቁ አብያተክርስቲያናትን እያሳየች ምጣኔ ሃብቷንም በዚሁ በምታገኘው ገቢ ትገነባለች፡፡

የላሊበላ ከተማዋ ነዋሪዎች የገቢ ምንጫቸው እና የሕይወት መሠረታቸው ቱሪዝም ነው፡፡ ታዲያ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች የላሊበላን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እየጎዳባት ነው፡፡ አስቀድሞ በኮሮና ቫይረስ፣ ቀጥሎ በወረራው ጦርነት የላሊበላ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በእጅጉ ተጎድቶ ቆይቷል፡፡ በመካከል በተፈጠረው ሰላም የላሊበላ ቱሪዝም እንደ ቀድሞውም ባይኾን እንኳን መነቃቃት ላይ ነበር፡፡ በቅርቡ በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት ደግሞ መነቃቃት ላይ የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሌላ ፈተና ኾኖበታል፡፡

ላሊበላ አሁን ሰላም ነች፡፡ ጎብኚዎቿንም ኑ ጎብኙኝ ብላለች፡፡ የቀደመው እንግዳ ተቀባይነቴ፣ የቀደመው መልካምነቴ ሳይለወጥ እጠብቃችኋለሁ፣ በክብር ተቀብዬ፣ በፍቅር አሰገብቼ በደስታ እሸኛችኋለሁ እያለች ነው፡፡

የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት አስተባባሪ ማንደፍሮ ታደሰ የላሊበላ የኢኮኖሚ ምንጭ እና የነዋሪዎቿ መሠረት ቱሪዝም መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስና የህውሓት የወረራ ጦርነት ላሊበላን በኢኮኖሚ ጎድቷት ማለፉንም አስታውሰዋል፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴዋ በመጎዳቱ በከተማዋ የነበሩ ባለሀብቶች እንዲለቁ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ በቱሪስት አስጎብኚ ማኅበር እና በባሕላዊ ማጓጓዣ የተሰማሩ አካላት ሥራቸውን እስከመቀየርና አካባቢውን ለቀው እስከመሄድ መድረሳቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ ከሕውሓት ጦርነት በኋላ ባገኘችው አንጻራዊ ሰላም ቱሪዝሙ ሙሉ ለሙሉ ባይሆን እንኳን መነቃቃት አሳይቶ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ቱሪስቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በቡድንም በተናጠልም ሲመጡ እንደነበር ያስታወሱት አሥተባባሪው በቅርቡ የተከሰተው ግጭት ከተማዋ ቱሪስቶችን እንድትናፍቅ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ ጎብኚዎችን ታሳቢ አድርገው የሚሠሩ ሆቴሎች አሁን ላይ ከሥራ ውጭ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ አሁን ላይ ሰላማዊ እንስቃሴ መመለሱንም ገልጸዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ እና የሰሜኑ ጦርነት በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚደረገውን ጥገና እንዳጓተቱትም ተናግረዋል፡፡ ለሰላም ሁሉም ሰው አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ መንግሥትም ጥያቄዎችን በስክነት እና በበጎነት በማየት ፈጣን እና ተገቢ ምላሽ በመስጠት ሰላምን ማጽናት ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

የትኛውም አካል በውይይት የማመንና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልምድ ሊያዳብር እንደሚገባው ነው የተናገሩት፡፡ የላሊበላ ነዋሪዎች እንግዳ የመቀበል፣ የመንከባከብ፣ አቅጣጫ የመጠቆም እና ሌሎች ጎብኚዎችን የሚጠቅሙ ነገሮችን የማድረግ የዳበረ ልምድ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ እንግዶች አካባቢውን እንዲጎበኙ እና የቆይታ ጊዜያቸው እንዲራዘም እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት፡፡

በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም መረጋገጥ አለበት ያሉት አስተባባሪው ሰላም ከሌላ በላሊበላ ያለው የኢኮኖሚ ውድቀትና ችግር እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡ ወደ ከተማዋ የአውሮፕላን በረራ እንዳለ የተናገሩት አስተባባሪው እንግዶች ከተማዋን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በከተማዋ እንግዶችን የሚጎዳ የሰላም ችግር አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡ እንግዶች የተለመደውን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በእንግዶች ላይ የሚደርስባቸው ስጋት አለመኖሩን ያነሱት አስታባባሪው ላሊበላን ኑ ጎብኟት ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ሂዱና ጎብኟት፣ ታሪክና ሃይማኖትን እዩባት፣ የረቀቀውን ጥበብ እያያችሁ ተደነቁባት፣ የኢትዮጵያን ክብርና ታላቅነት አድንቁባት፡፡ የአበውን ብልሃት እያያችሁ ተደመሙባት፡፡ ታሪክንም ለዓለም ሁሉ ንገሩባት፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የዕርድ እንስሳት ድጋፍ አደረገ።
Next articleሰሞኑን ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት አሻቅቦ የነበረው የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች ዋጋ ወደ ነበረበት እየተመለሰ ነው፡፡