“ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይገባል” የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኅላፊ እና የጎንደር ቀጣና የኮማንዶ ፖስት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው

72

ጎንደር: ነሐሴ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ በከተማዋ ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሕዝብን ጥያቄ ተቀብሎ በተገቢው መንገድ መመለስ መቻል አስፈላጊ ስለመኾኑ በውይይቱ ተናግረዋል።

በመድረኩ አንድነትን ማጠናከር እና በኅብረት መቆም ተገቢ ስለመኾኑ የተነሳ ሲኾን ተቀራርቦ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ ተመላክቷል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እና የጎንደር ቀጣና ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ባዩህ አቡሀይ በመድረኩ የተነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ስለመኾናቸው አፅንኦት ሰጥተው የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልፀዋል። ኾኖም እንደ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚቀርቡበት እና ችግሮች የሚፈቱበት መንገድ ጥንቃቄ የተሞላበት መኾን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኅላፊ እና የጎንደር ቀጣና የኮማንዶ ፖስት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሥራ ኀላፊዎች ሥራዎችን እየከወኑ ነው ብለዋል። ችግሮችን ከግጭት ይልቅ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ተገቢ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጥገና በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ
Next articleየደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የዕርድ እንስሳት ድጋፍ አደረገ።