“የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጥገና በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ

77

ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተመረጠ ሥፍራ የተመረጠ፣ በድንቅ ጥበብ፣ በረቂቅ የእጅ ሥራ የተቀመጠ፣ ታላቅ ቤተ መንግሥት፡፡ ታላቁን ሐይቅ ጣናን በአሻገር ያዩበታል፣ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ወይዛዝርቱ፣ ልዑላን ኀያላኑ፣ የጦር አበጋዞቹ ሁሉ ስለ ሀገር አንድነት፣ ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት መክረውበታል፡፡ ለአንዲት ሀገር ክብር፣ ለአንዲት ሠንደቅ ፍቅር እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ በአንድነት ወስነውባታል፡፡

ንጉሡ፣ ንግሥቷ፣ መኳንንቱና፣ መሳፍንቱ፣ ልዑላኑ፣ ሊቃውንቱ በግርማ ታይተውበታል፣ በግርማም ኖረውበታል፡፡ ባለ ግርማ ሀገርም ለልጅ ልጅ አጽንተውበታል፡፡ የአጼ ሠርጸ ድንግል አሻራ፣ የነገሥታቱ ማረፊያ፣ ቅንጡው ቤተ መንግሥት ጉዛራ፡፡

በሚያምር ቦታ የተሠራ ድንቅና ብርቅ ቤተ መንግሥት ይሉታል፡፡ንጉሡ ገዳማት፣ አድባራት፣ ቅዱሳን መነኮሳት የሚኖሩበትን፣ ቅዱሳን መጻሕፍት የመሉበትን፣ ምስጢር የበዛበትን፣ ጣናን እየተመለከቱ የሚኖሩበት ፎቅና ምድር ያለው ቤተ መንግሥት አነጹ፡፡ ያም ቤተ መንግሥት እጹብ ድንቅ አስባለ፡፡ አምሳያ የለሽ እየተባለም ተዘመረበት፡፡ ግርማውና ውበቱም ዛሬ ድረስ ከእርሱ ጋር አለ፡፡ ዛሬም የተመላለሱበትና ዙፋን ላይ የተቀመጡበት ነገሥታት፣ መኳንንት፣ መሳፍንት በውስጡ ያሉ ይመስላል፡፡

ቅንጡው ቤተ መንግሥት ግርማው ዛሬም ድረስ አብሮት ይኑር እንጂ ጥንካሬው ግን በዘመን ብዛት ቀንሷል፡፡ ረዘም ያለ ዓመታትን በግርማና በክብር የቆየው የጉዛራ ቤተ መንግሥት በዚህ ዘመን ልጆቹ እንዲደግፉት፣ ግርማውን እና ክብሩን እንዲጠብቁለት ፈልጓል፡፡ በእድሜ እርዝመትና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ቤተ መንግሥቱ ጉዳት ደርሶበት ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ቤተ መንግሥቱ ታሪክን እየዘከረ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር የጥገና ሥራ እየተሠራለት ነው፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አቤል መብት የጉዛራ ቤተ መንግሥት በኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን አማካኝነት የጥገና ሥራው እየተሠራለት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ወቅታዊ የሰላም እጦት ቢያጋጥምም ከጥቂት ቀናት ውጭ የከፋ መስተጓጎል እንዳልፈጠረባቸው ነው የተናገሩት፡፡ ጥገናው አሁን ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ አካባቢው ሰላማዊ በመኾኑ ሥራውም በጥሩ ሁኔታ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡

በተፈለገው የጊዜ ገደብና በሚጠበቀው የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ጥገናው የቅርሱን ታሪካዊ ዳራ ጠብቆ የሚከናወን መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ለጥገናው 35 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተያዘለትም አስታውቀዋል፡፡ ሥራው በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ እቅድ ተይዞለት እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ ጥገናው ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ እንዲጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሥራው አስተማሪ በኾነ መልኩ በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገበት መኾኑን አንስተዋል፡፡

ለጥገና አገልግሎት የሚውሉት ቁሳቁስ የቅርሱን ታሪካዊ ዳራ የሚጠብቁ፣ በባለሙያዎች ጥናትና ሙከራ እየተደረገባቸው የሚሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ቤተ መንግሥቱን የሚመጥን ቁሳቁስ እንደሚቀርብም ተናግረዋል፡፡ ኖራውና እንጨቶቹ ከዚያ ዘመን ጋር ተመሳሳይ እንዲኾኑ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ጉዛራ ቤተ መንግሥትን መጠገን ታሪክን ከማስቀጠል ባለፈ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጥቅሞችን ይዞ እንደሚመጣም ተናግረዋል፡፡

ጥንታዊ ቅርሶቹ እንዲጠገኑ፣ የቱሪስት መዳረሻዎች ጎብኚዎችን እንዲስቡ ሰላምን ማስጠበቅ ይገባልም ብለዋል፡፡ ያለ ሰላም የሚሳካ የቱሪዝም ሥራ አለመኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ እንደ ክልልም ኾነ እንደ ሀገር የሚፈጠሩ ችግሮችን በወግና በባሕላችን መሠረት በሰላም መፍታት ይገባልም ብለዋል፡፡ የሰላም እጦት ሀገርና ሕዝብን በእጅጉ እንደሚጎዳም አመላክተዋል፡፡

ሁሉም ስለሰላም መስበክና ስለ ሰላም መሥራት እንደሚገባው የተናገሩት ኀላፊው ሰላም ሲኖር ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንደሚመጡም ተናግረዋል፡፡ የሰላም ጉዳይ የሁሉም ሰው ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ችግሮችን በስክነት እና በብልሃት መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ስለ ሰላም በእጅጉ ሊሠሩ ይገባቸዋልም ነው ያሉት፡፡

ሰላም የሁሉ እንደኾነ ሁሉ ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ መስጠት አለበት ብለዋል፡፡ የሰላም እጦት ሲኖር ሀገር ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ እንደምታጣና በቱሪዝም ዘርፍ ማሳካት የሚገባትን የምጣኔ ሃብት እድገት ማሳካት እንደማትችልም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም እጦቱ የሀገር ማስቀጠያ ድልድይ የኾኑትን እናቶች የበለጠ ተጎጅ ስለሚያደርግ ሁሉም ወገን ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለሱ የሥነልቦና ምሁር አሳሰቡ፡፡
Next article“ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይገባል” የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኅላፊ እና የጎንደር ቀጣና የኮማንዶ ፖስት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው