የሰላም እጦቱ የሀገር ማስቀጠያ ድልድይ የኾኑትን እናቶች የበለጠ ተጎጅ ስለሚያደርግ ሁሉም ወገን ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለሱ የሥነልቦና ምሁር አሳሰቡ፡፡

50

ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የልጅነት እንክብካቤ ትምህርት ክፍል ኀላፊ ዶክተር እባቡሽ ይርዳው እንዳሉት በሰላም እጦት ጊዜ ቅድሚያ ተጎጅ የሚኾኑት እናቶች ስለመኾናቸው አስረድተዋል፡፡

የእናቶች ቤተሰባዊ ጫና ካለው የቤተሰብ አባል አኳያ ይለያል የሚሉት ዶክተር እባቡሽ የሰላም እጦት በሚኖርበት ጊዜ እንደማንኛውም ሰው ካለባቸው ስጋት በተጨማሪ ልጆቻቸው ሲጨነቁ እና ስጋታቸውን እያዩ የበለጠ ተጎጅ እንደሚኾኑ ነግረውናል፡፡

ሰላም ሲርቅ እናቶች ለበለጠ ጭንቀት ስለሚዳረጉ ለአእምሮ ጭንቀት እንደሚዳረጉም መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ነው ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ የነገሩን፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚያልፉ እናቶች ብዙ ጊዜ ቤተሰብ የመምራት እና የመንከባከብ ችግሮችም ሊገጥማቸው እንደሚችል ነው ያስገነዘቡት፡፡

የሰላም እጦቱ በእናቶች ስብዕና ላይም የራሱን አሉታዊ ጯና እንደሚያሳርፍም ነው ዶክተር እባቡሽ ያብራሩት፡፡ በተለይም በሰላም እጦት ለረዥም ጊዜ የሚያሳልፉ እናቶች ከተፈጥሯዊ የጤና እክልም አኳያ የራሱ ተጽእኖ እንደሚያሳድርም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም የወር አበባቸው የሚዛባበት፣ ለድብርት የሚጋለጡበት እና ለበለጠ ጉዳት የሚዳረጉበት ሁኔታም እንዳለ ነው ዶክተር እባቡሽ የነገሩን፡፡

እናቶች በተለያዩ የሰላም መደፍረሶች ምክንያት ስብዕናቸው ሲጎዳ በተመሳሳይ በሚያሳድጓቸው ልጆችም ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው እና የተሻለ ሀገር ተረካቢ ዜጋ የማፍራት እድላቸውም እየቀነሰ እንደሚመጣም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በሰላም እጦት ችግር ውስጥ በወደቁ ወላጆች ያደጉ ልጆች ደግሞ አዋቂዎች ሲኾኑ በአስተሳሰብ ወደ ኋላ የቀሩ የመቅረት እድል እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል፡፡ በምርት እና ምርታማነት ላይ የራሱ ጉዳት እንደሚያስከትልም አብራርተዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ጉዳይ ደግሞ አንድ ቦታ ላይ ማቆም ካልተቻለ የበለጸገ ሀገር የመገንባት ህልምን እንደሚያጨናግፍ ነው የገለጹት፡፡

አሁን ላይ በተፈጠረው የሰላም እጦት ዋና ተጎጅዎች እናቶች እና ቀጣዩ ትውልድ በመኾኑ ሁሉም እነዚህን አካላት ታሳቢ አድርጎ ከግጭት ይልቅ ወደ ሰላማዊ ውይይት መምጣት ቢችል ሲሉ መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ትራንስፖር የሰላም ምልክት እና ተምሳሌት ነው”
Next article“የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጥገና በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ