“ትራንስፖር የሰላም ምልክት እና ተምሳሌት ነው”

82

ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ሳምንታት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት በርካታ የመሰረተ ልማት ተግባራት አገልግሎት መስጠት አቋርጠው ነበር፡፡ አለመረጋጋቱ ከፈጠረው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በተጨማሪ የማኀበራዊ አገልግሎት መቋረጥ በበርካታ ዜጎች የእለት ከእለት ሕይዎት ላይ ጉዳት አስከትሏል፡፡

የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ ከተቋረጡ የማኀበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መካከል የትራንስፖርት ዘርፉ አንዱ ነው፡፡ በክልሉ በበርካታ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደ ሥራ መመለስ መጀመሩን የክልሉ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

“ትራንስፖርት የሰላም ምልክት እና ተሳሌት ነው” ያሉን በትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦት እና ስምሪት ዳይሬክተር አቶ ጋሻው ተቀባ ናቸው፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር በአካባቢው ሰላም ለመስፈኑ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል ያሉት ዳይሬክተሩ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች አገልግሎቱ ወደነበረበት ሰላማዊ ኹኔታ ተመልሷል ብለዋል፡፡

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቱ መጀመር መልካም ኾኖ ሳለ ተገልጋዮች ሕጋዊ ባልኾነ መልኩ የዋጋ ጭማሪ ይደረግባቸው እንደነበር ያነሱት አቶ ጋሻው ችግሩን ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎ መሻሻሎች ታይተዋል ብለዋል፡፡ በተገልጋዩ ሕዝብ እና በአገልግሎት ሰጪዎቹ መካከል የሚገቡ ሕገ-ወጥ ደላሎች ከመናኽሪያ እንዲወጡ እየተሠራ እንደኾነም ነግረውናል፡፡

መጪው ጊዜ በዓል መኾኑን ተከትሎ ከፍተኛ የሕዝብ ፍሰት ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል ያሉት አቶ ጋሻው በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የትራፊክ ፖሊሶችን ጨምሮ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ይደረጋል ተብሏል፡፡
ተገልጋዩ ሕዝብም የሚስተዋሉ ውስንነቶችን እና ሕገ-ወጥ ተግባራትን በየመናኽሪያዎቹ ለሚገኙ የስምሪት ባለሙያዎች መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአረንጓዴ ጎርፍ ፍሰት በቡዳፔስት!
Next articleየሰላም እጦቱ የሀገር ማስቀጠያ ድልድይ የኾኑትን እናቶች የበለጠ ተጎጅ ስለሚያደርግ ሁሉም ወገን ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለሱ የሥነልቦና ምሁር አሳሰቡ፡፡