የአረንጓዴ ጎርፍ ፍሰት በቡዳፔስት!

72

ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምንጊዜም ቢሆን ዓለም የአትሌቲክስ ድግስ እንዳላት ሲሰማ በርካቶች ይኽንን ትዕይንት አብዝተው ይናፍቁታል፡፡ እልክ አስጨራሽ ፉክክር፣ ለሀገር ክብር የሚከፈል የቡድን ሥራ፣ ለሰንደቅ ዓላማ ልዕልና የሚውል ገፀ-በረከት እና ተመልካችን ቁጭ ብድግ የሚያደርግ የአልሸነፍም ባይነት ፍልሚያ የድባቡን ቀልብ ይስባል፡፡ ዓለም አቀፉ የስፖርት ቤተሰብ ኢትዮጵያን በአትሌቲክስ መድረክ ስታሸንፍ መመልከት ሁሌም ይናፍቃል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ ውድድሮች በተለይም ደግሞ የረጂም ርቀት ሩጫ የኢጋድ ፉክክር እስኪመስል ድረስ ምሥራቅ አፍሪካዊያኑ ሀገራት አንገት ለአንገት ይተናነቁበታል፡፡

በውድድሩ የካበተ ዝና ያላት ኢትዮጵያ የፖን-አፍሪካኒዝም ምልክት የኾነውን ሰንደቋን በየውድድሮቹ ፍጻሜ ላይ ከፍ አድርጋ ስታውለበልብ በርካቶች በደስታ እምባ ይርሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ የሌለችበት የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ምን ያክል ጎዶሎ ሊኾን ይችላል እስኪባል ድረስ የመድረኩ ኮኮብ ሀገር ትሆን ዘንድ ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ ልጆቿ ብርቱ ትግል አድርገዋል፡፡

ከሮም እስከ ቶኮዮ፣ ከበርሊን እስከ ዶሃ፣ ከሞስኮ እስከ ኦሳካ፣ ከፓሪስ እስከ ኤድመንተን፣ ከለንደን እስከ ሲድኒ፣ ከሄልሲንኪ እስከ ቡዳፔስት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች “አረንጓዴ ጎርፍ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ግማሽ ምዕተ ዓመታትን ሊያስቆጥር ጥቂት ዓመታት ብቻ በቀሩት የዓለም አትሌቲክስ የውድድር መድረክ ውስጥ ኢትዮጵያ ለዓለም የስፖርት ቤተሰቡ አይረሴ ትዝታ አስቀምጣለች፡፡

ከአበበ ቢቀላ እስከ ኃይሌ ገብረሥላሴ፤ ከቀነኒሳ በቀለ እስከ ስለሺ ስህን፣ ከአሰፋ መዝገቡ እስከ ሚሊዮን ወልዴ በወንዶቹ፡፡

ከደራር ቱቱሉ እስከ ጌጤ ዋሜ፣ ከጥሩነሽ ዲባባ እስከ መሰረት ደፋር በሴቶቹ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለዓለም የአትሌቲክስ ውድድር አፍቃሪዎች የደስታ ምንጭ ኾነዋል፡፡ ከግል ክብራቸው እና ጥቅማቸው በላይ የሀገራቸውን ክብር እና ጥቅም የሚያስቀድሙት ልጆቿ በየውድድር መድረኮቹ የሚያሳዩት የቡድን ሥራ በርካቶችን እምባ ያራጫል፤ ተሸናፊዎቹን ሀገራትም ያስቆጫል፡፡

አበበ በቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፍ የዓለም አትሌቶች የጽናት ተምሳሌት ኾኖ አለፈ፡፡ ኃይሌ ከሌላ ፕላኔት የመጣ ሰው ነው እስኪባል ድረስ በቡጢ እየተነረተ እንኳን አሸንፎ ከሰንደቋ ስር በእምባ ታጠበ፡፡ የኃይሌ ማሸነፍ ሳይኾን መሸነፉ ነው ዜና የሚኾን እስኪባል ድረስ ደግሞ ደጋግሞ በማሸነፍ አጃኢብ አሰኛቸው፡፡

ቀነኒሳ ባለባቸው ውድድሮች መሳተፍ ሁለተኛ ለመውጣት ነው እስኪባልለት ድረስ ሀገሩን ከከፍታ ማማ ላይ አወጣት፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ የዓለም አትሌቲክስ ውድድሮች ክስተት ኾነች፡፡ ይኽ ሁሉ የሀገሪቱ ትናንት ያለፈ ነገር ግን መቼም ቢኾን ሊዘነጋ የማይችል የስፖርት ቤተሰቡ ትዝታ ነው፡፡
19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ትናንት በሃንጋሪዋ ቡዳፔስት ሲጀመር ኢትዮጵያዊያኑ ዛሬም እንደ ትላንቱ ሁሉ የዓለምን ሕዝብ ዓይን እና ጆሮ ስበው አምሽተዋል፡፡

የሴቶቹ 10 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ዓለም የናፈቀውን የአረጓዴ ጎር ፍሰት በቡዳፔስት ተመልክቷል፡፡

ከወርቅ እስከ ነሐስ ያሉትን ሜዳሊያዎች በመጠራረግ በዚያ የዓለም ሀገራት የሰንደቅ ከፍታ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የሀገራቸው ሰንደቅ ብቻውን እንዲውለበለብ አድርገዋል፡፡
ጉዳፍ ፀጋየ፣ ለተሰንበት ግደይ እና እጅጋየሁ ታየ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተከታትለው በገቡበት የምሽቱ ውድድር ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፋን ሃሰን አሳዛኝ ተሸናፊ ኾናለች፡፡

ለመጨረሻ ጊዜ በሴቶቹ የውድድር መድረክ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተከታትለው በመግባት የአረንጓዴ ጎርፍ ፍሰት የታየው 2001 ካናዳ ኤድመንተን በተደረገ ውድድር ነበር፡፡ በወቅቱ ደራር ቱሉ፣ ብርሃኔ አደሬ እና ጌጤ ዋሜ የዘመኑ አረንጓዴ ክስተት ነበሩ፡፡ ዛሬ ደግሞ በጉዳፍ፣ ለተሰንበት እና እጅጋየሁ ጥምረት ኢትዮጵያ ውድድሩን በድል ጀምራለች፡፡ በቀጣዮቹ 9 ቀናት ከቡዳፔስት ምን ይሰማል የሚለውን አብረን እናያለን፡፡

መልካም እድል ለኢትዮጵያ!

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበግጭት ሰበብ የሕዝብ መጠቀሚያ ተቋማት እና ንብረቶችን ማውደም ተገቢ አለመኾኑን የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
Next article“ትራንስፖር የሰላም ምልክት እና ተምሳሌት ነው”