
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከባሕርዳር ከተማ የተለያዩ ቀበሌዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች በወቅታዊ የከተማዋ እና የክልሉ ኹኔታ ላይ ውይይት እና ምክክር አካሂደዋል።
በውይይቱ ላይ በክልሉ የተረጋጋ እና ፍጹም ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስፈን በሕዝብ እና በመንግሥት መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች ተነስተዋል።
በነዋሪዎች ከተነሱ ሃሳቦች መካከል፦
👉 በግጭት እና መገዳደል የሚፈታ ችግር ባለመኖሩ ችግሮችን በመወያየት ብቻ በፍጥነት መፍታት ያስፈልጋል።
👉ሀገራዊ አንድነትን በመጠበቅ ከጦርነት፣ ከችግር እና ከጉስቁልና የተላቀቀች ሀገር ለመመስረት ሁሉም መትጋት አለበት
👉የተከሰተውን ግጭት እና አለመረጋጋት በአንድነት ቆመን በፍጥነት እልባት በመስጠት የኢትዮጵያን ክፉ የሚሹ አካላትን እናሳፍር
👉መንግሥት ሕዝብ ለሚያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ተገቢውን እውቅና መስጠት እና አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት
👉ሕዝብን የሚያማርሩ እና ለቁጣም የሚያጋልጡ የቆዩ የመልካም አስተዳደር እጦት ችግሮች በየደረጃው በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው
👉በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች መንግሥትን ከሕዝብ ከሚያቃቅር እና ጥላቻን ከሚሰብክ ንግግር መቆጠብ አለባቸው
👉 የአማራ ክልል ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊትን ደጀንነት እና የሀገር አለኝታነት ጠንቅቆ ይረዳል፤ የሠራዊቱ አባላትን ከሕዝቡ ለመነጠል የሚደረገው አሉባልታ በፍጥነት መቆም አለበት
👉 አለመረጋጋቱን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሕዝብን ለተጨማሪ ጫና ያጋለጡ ስግብግብ ነጋዴዎች በሕግ ሊጠየቁ ይገባል
👉በየአካባቢው የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ሊፈጠር የሚችልን ወንጀል ኅብረተሰቡ ለራሱ ሰላም ዘብ በመኾን መከላከል ይገባል።
👉 የተከሰተው አለመረጋጋት አስቸኳይ እና ዘላቂ እልባት እንዲያገኝ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እስከታች ወርደው ሕዝቡን ፊት ለፊት ማወያየት አለባቸው
👉 ሕዝብን የሚበድል አመራር ሲያጋጥም ነቅሶ በማውጣት የማረም ብሎም በሕግ የመጠየቅ ባሕል መዳበር አለበት፤ በአመራር ላይ የሚደርስ ስድብ እና ክብር መንካት እንዲሁም የደቦ ፍርድ በአስቸኳይ እና በዘላቂነት ይቁም ተብሏል።
ውይይቱን የመሩት የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አደራ ጋሼ እና የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር አትንኩት አያሌው ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ አደራ በነዋሪዎች የተነሱ ሃሳብ እና አስተያየቶችን በመውሰድ እና የእቅድ አካል በማድረግ እንሠራለን ብለዋል። ሀገርን ለማዳን መነጋገር እና መወያየት አስፈላጊ ስለመኾኑም ገልጸዋል። ሕዝብን ወደ ግጭት እና አለመረጋጋት የመሩ ጥያቄዎች በፍጥነት እንዲፈቱ ሁሉም በየደረጃው የድርሻውን ወስዶ ይሠራልም ብለዋል። “ስንከባበር፣ ስንደማመጥ እና የዳበረ ኢኮኖሚ ስንገነባ ለጥያቄዎቻችን ሁሉ መልስ ለማግኘት ምቹ ኹኔታ ይፈጠራል” ሲሉም አቶ አደራ አስረድተዋል።
ረዳት ኮሚሽነር አትንኩት አያሌው በበኩላቸው በባሕርዳር ከተማ ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት የሰው ሕይወት ማለፉንና ንብረትም መውደሙን ጠቁመው፤ በግጭቱ ወቅት የሕዝብ እና የሀገርን ሃብት አላስነካም ብለው በመታገል ጠብቀው ያተረፉ በርካታ ነዋሪዎች መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡
ምስጋናም አቅርበዋል። ኮሚሽነር አትንኩት ባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎቿ ለልማት የቆሙ፤ ሰላማቸውም የተጠበቀ እንዲኾን በትኩረት እንሠራለን ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በሕዝቡ መካከል እየገቡ ለክልሉ እና ለሀገር ዘላቂ ሰላም በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!