
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከትናንቱ የሚማር ከተገኘ ዓለም እጅግ አስከፊ እና መራር የጦርነት ታሪክ አላት፡፡ በእያንዳንዱ ሀገር የታሪክ ማጀት ውስጥ ጊዜ ወስደን ብንመረምር ለህልውናቸው ስጋትን ለሕዝቦቻቸው ፍርሃትን የፈጠሩ የጦርነት ታሪኮቻቸውን ፈልፍለን እናወጣለን፡፡ ከሁሉም ሀገራት የጦርነት ታሪክ የሚመዘዝ አንድ ሃቅ ቢኖር ደግሞ ሁሉም ጦርነት መቋጫውን እና ፍጻሜውን የሚያገኘው በውይይትና በሰላም ስምምነት መሆኑን ነው፡፡
ዛሬ ላይ በሦስተኛው ዓለም ሀገራት የጦርነት ክስተት ውስጥ ሁሉ እጅግ የረዘመ እጅ አላቸው የሚባሉት በርካቶቹ ምዕራባዊያን ሀገራት ትናንት አስከፊ እና ጨፍጫፊ የተባለላቸውን ጦርነቶች አስተናግደዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በብሂላቸው “የሰው ልጅ አንድም በቀለም ‘ሀ’ ብሎ ወይም በመከራ ‘ዋ’ ብሎ ይማራል” እንደሚሉት በርካቶቹ ሀገራት በምርምር ካመጡት ለውጥ ይልቅ በጦርነት ያሳለፉት እንግልት ሳያስተምራቸው አልቀረም፡፡
አውሮፓዊያን “ከዌስት ፋሊያ” የሰላም ሰምምነት ላይ እስኪደርሱ ድረስ ለሦሥት አስርት ዓመታት ያልተቋረጠ ጦርነት ውስጥ እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል፡፡ በበርካታ ምዕራባዊያን ሀገራት ከ1618 እስከ 1648 (እ.አ.አ) በዘለቀው ጦርነት ከ8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሕይዎታቸው አልፏል፣ እልፎች ለስደት ተዳርገዋል እንዲሁም ከተሞች ዶግ አመድ ሆነው ወድመዋል፡፡ዛሬ የሚታዩት ቅንጡ እና ቀልብን የሚስቡ ከተሞቻቸው ትናንት የጦርነት አውድማ ሆነው እሳት አበራይተው አመድ የሚያመርቱ ምድራዊ ሲኦል ነበሩ፡፡ የጦርነቱ ተሳታፊ ሀገራት ከስሜት ወጥተው በስሌት፤ ከግጭት ርቀው በትዕግስት ነገሩን ሲመለከቱት ጦርነቱ የሚጠናቀቀው በጦርነት ሳይሆን በስምምነት እንደሆነ ተገለጠላቸው፡፡ ግጭትን ተመልሰው ላያስቡት፤ ጦርነትን ከእንደገና ላይሞክሩት በሚያስችል መልኩ በአፈሙዝ የጀመሩትን ጨዋታ በብዕር አጠናቀቁት፡፡ ዛሬ ላይ ሁሉም ምዕራባዊያን ሀገራት ከጦርነት ፍጹም ነጻ ናቸው ባይባልም እንኳ ቢያንስ እርስ በእርስ ከሚያባላ እና ትርፍ አልባ ጦርነት ተገላግለዋል፡፡
እንደ ምዕራባዊያኑ የዘመን ስሌት ከ1964 ጀምሮ ኮሎምቢያ ከቬንዚዮላ ጋር በሚያዋስናት ድንበሯ አካባቢ ያጋጠማት የእርስ በእርስ ጦርነት ዓለም ካስተናገደቻቸው የከፉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች መካከል አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ በሀገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት እና በፋርክ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ግጭት ውሎ ሲያድር እየተካረረ መጥቶ ኮሎምቢያዊያንን ለከፋ መከራ ዳርጓቸው ነበር ይባላል፡፡
ግጭቱን ይበልጥ ያባባሰው እና እንዳያባራ ያደረገው ደግሞ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ያየለበት መሆኑ እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ከ54 ዓመታት በላይ የዘለቀው የኮሎምቢያዊያን የእርስ በእርስ ግጭት በሰላም እንዲጠናቀቅ ከ2002 እስከ 2010 (እ.አ.አ) ድረስ ሀገሪቷን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አልቫሮ ኡርቤ ሚናውን ወሰዱ፡፡ ምንም እንኳን የፕሬዚዳንት ኡርቤ የሰላም ጥረት መቋጫ ሳያገኝ በፕሬዚዳንት ማኑኤል ሳንቶስ ቢተኩም አዲሱ ፕሬዚዳንት የኡርቤን የሰላም ጥረት ተቀብለው 2018 ላይ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሀገሪቱን ወደ መቀመቅ ያወረዳትን ግጭት በሰላም ቋጩት፡፡ ዛሬ ላይ ኮሎምቢያዊያን ያንን የከፋ የመከራ ዘመን መድገም ቀርቶ ማሰብ እንኳን የሚፈልጉ አይመስሉም፡፡
በርካታ የዓለም ሀገራት አንድ ወቅት የገጠማቸውን የጦርነት ታሪክ ዳግም ላይመጣ ምዕራፉን ቋጭተው ሰላምን አስፍነዋል፡፡ አንዳንዶቹ በተለይም ደግሞ በርካቶቹ የሦስተኛው ዓለም ሀገራት ደግሞ ትናንት ካሳለፏቸው በርካታ የጦርነት ታሪኮች መማር ተስኗቸው ዛሬም እንደ አዲስ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስሙ እንሰማለን፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት የፈጠረው ስደት፣ ረሃብ፣ ኋላቀርነት፣ ጉስቁልና እና መከራ መለያቸው እስኪመስል ድረስ ከተጣባቸው ፍዳ መላቀቅ የተሳናቸው ሀገራት የበዙ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ጥንታዊ ከሚባሉት ሀገራት ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ ሀገሪቱ የረጅም ዘመናት እርሾ ያካበተ የመንግሥት አስተዳደር፣ ጥንታዊ መሰረት ያለው እምነት፣ የከበረ አስተምህሮ እና ቅቡል እሴቶች ቢኖሯትም ለብዙ ዘመናት ከሚጎበኛት የጦርነት ታሪክ መሻገር ግን አልቻለችም፡፡ የትውልድ ክፍተት የሚፈጥር ጦርነት፣ አብሮነትን የሚጎዳ የእርስ በእርስ ግጭት እና ያላባራ እልቂት የታሪኳ አንድ አካል እስኪመስል ዛሬም ድረስ ደግሞ ደጋግሞ ግጭት ሲጎበኛት ይስተዋላል፡፡
በተለይም 1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እንደ አዲስ የታየው ብሔር ተኮር እሳቤ እና አዝማሚያ ነባሩን አብሮነት ክፉኛ ሸረሸረው፡፡ መርጠው የሚያለቅሱ፤ ለይተው የሚያስለቅሱ የፖለቲካ ልሂቃን አብሮ የኖረውን የሀገሬውን ሰው የመከራ ፍዳ አበሉት፡፡ ከኖረበት ቀዬ የሚፈናቀል፣ የሚሰደድ እና የሚሞተው አርሶ አደር በዛ፡፡ ፍቅር በጥላቻ ሰከረ፤ አብሮነት በልዩነት ከሰረ፡፡ እልፎች በማያውቁት እና ባልነበሩበት ጉዳይ ውድ ዋጋ ከፈሉ፡፡ የጦርነት ምዕራፍ ተዘግቶ የሰላም መዝገብ በኢትዮጵያ የሚጀመረው መቼ ነውʔ ኢትዮጵያዊያን የግጭትን አስከፊነት እስኪረዱ ምን ያክል የሕይዎት ዋጋ መክፈል ግድ ይላቸዋልʔ ከሩዋንዳ እና ከካናዳ፤ ከኮሎምቢያ እና ከዩጎዝላቪያ የምትማረው መቼ ነውʔ ከታላቅነት ጉዞዋ የገታትን፤ ከቀደምትነት መንበሯ ያንሸራተታትን የግጭት ምዕራፍ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት “ኢትዮጵያስ መቼ ይሆን የምትማረው?”
ምንጭ፡- ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!