
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለዘመናት ሕግና ሥርዓት የጸናባት፣ ጥበብ የሚፈልቅባት፣ እሴት የጠነከረባት፣ ኃያላን ነገሥታት የነገሡባት፣ ጥበብና ብልሃት የተቸሩ ሹማምንት የኖሩባት፣ ምስጢር የሚያሜሰጥሩ፣ ነገን በጥበብ የሚናገሩ፣ ከራስ ትውልድ አልፎ ለዘመናት ለሚቀጥል ትውልድ ድንቅ ታሪክ ያኖሩ ጠቢባን የተገኙባት ኢትዮጵያ ሰላምን አብዝታ ትሻለች፡፡
ጀግኖቿ በደምና በአጥንታቸው ያጸኗት፣ ሽንፈት የማያውቃት፣ ጠላት አብዝቶ የሚፈራት፣ ኃያላን ነን ያሉ ሁሉ እጅ የሚነሱላት፣ ለክብሯ ስጦታ የሚያበረክቱላት፣ ጦር ሰብቀው ሊወጓት የተነሱት፣ በክብሯ ላይ ለመሳለቅ ወሰን ለመሻገር የፈለጉት ሁሉ ድል የሆኑባት፣ በሰርክ ጸሎትና ምልጃ የሚደርስባት፣ አምላክ የሚጠብቃት፣ ለምስክርነት ያስቀመጣት፣ ለምድር የተሰጠው ጸጋና በረከት ሁሉ ያለባት፣ ቅዱሳን የሚኖሩባት፣ ጀግኖች የሚወለዱባት ኢትዮጵያ ሰላምን ትፈልጋለች፡፡
ነጻነት በደምና በአጥንት የጸናባት፣ ቀኝ ገዢ ያፈረባት፣ የጥቁር ዘር ሁሉ የሚኮራባት፣ የነጻነት ምልክት፣ የአሸናፊነት ዓርማው የሚያደርጋት ኢትዮጵያ ሰላምና ሰላማውያንን ትፈልጋለች፡፡
ሠንደቋ በሰማይና በምድር የሚውለበለብላት፣ ሠንደቋን አስቀድመው የሚሄዱት ሁሉ ድል አድርገው የሚመለሱባት ኢትዮጵያ ሰላም ትሻለች፣ ሰላማውያንንም ናፍቃለች፡፡
የሰላም እመቤት የተባለች፣ እንደ ሮማን ፍሬ ሁሉን የያዘች የተሰኘች፣ በአምላክ ጥበብ የተዋበች፣ ግርማና ሞገስን የተላበሰች፣ ሰላምና ፍትሕ ያለባት ተብላ የተወደደች ኢትዮጵያ ሰላምን አብዝታ ትሻለች፡፡
የደከሙት የሚያርፉባት፣ የተራቡት የሚጠግቡባት፣ የታረዙት የሚለብሱባት፣ የተጠሙት የሚጠጡባት፣ መድረሻ ያጡ የተቅበዘበዙ የሚጠለሉባት፣ ጊዜ የገፋቸው፣ ዘመን ያዘመማቸው ጊዜና ዘመንን የሚያሳልፉባት ኢትዮጵያ ሰላምን ናፍቃለች፡፡
ለዘመናት በሰላም የኖረች፣ በሰላምም ሕገ እግዚአብሔርን እና ሕገ መንግሥትን ያከበረች፣ በሰላምም ጥበብን በሰው ልጆች ልብ ያረሰረሰች፣ ዕውቀትን እንደ ዥረት ያፈሰሰች ኢትዮጵያ አሁን ሰላምን ተጠምታለች፤ ሰላማውያንንም ተርባለች፡፡
የጥበብ እመቤት ተብላ የተጠራችው፣ የፍትሕ አድባር የተባለችው፣ ፍትሕ ዐዋቂ ንጉሥ የሚነግሥባት የተሰኘችው አሁን ሰላምን እና ሰላማውያንን ተርባለች፡፡ በታሪኳ ሰላማዊ እንደኾነችው ኹሉ አሁንም ወደፊትም በሰላሙ በትር የመከራውን ባሕር ትከፍላለች፣ በሰላሙ ዙፋን ጸንታ ትቀመጣለች፣ በሰላሙ ዘውድ አምራና ተውባ ትኖራለች።
ያቺ ፍትሕ የበዛባት፣ ፍትሐዊ ንጉሥ የነገሠባት፣ እንግዳ ተቀባዮች፣ ኩሩዎች፣ ጀግኖች እና ታማኞች የሚኖሩባት ፣ የሰላም ርግብ የተባለች ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ሰላም ትፈልጋለች፡፡ የአሁኗ ኢትዮጵያም ያ ደግ ዘመን ይመጣ ዘንድ ልጆቿን በለቅሶ ድምጽ ትጣራለች፣ ኑ ተዋደዱ፣ የሰቆቃውን ድምጽ አጥፉት ለዓመታት የሚፈስሰውን እንባዬን አብሱት፣ የቀደመ መልኬን፣ የድሮ ደም ግባቴንና መወደዴን መልሱት እያለች እየተጣራች ነው፡፡ ኑ የክብሬን ካባ ደርቡት፣ በፍቅርና በአንድነትም ኑሩበት እያለች ትጣራለች፡፡ ለዘመናት የማይጠፋና የማይጠወልግ ፈገግታ ናፍቋታልና፡፡
“ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፣ እርሱም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ ” እንዳለ መጽሐፍ እርስ በእርስ መነካከስ፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ መነሳት ኢትዮጵያውያንን አማርሯቸዋል፣ መከራና ስቃይ አብዝቶባቸዋል፡፡ ሕዝቦቿም እርስ በእርስ እንዳይጠፋፉ፣ ምድሯም የማያልቅ መከራ እንዳይመጣባት የሚጠነቀቁበት ዘመን ላይ ናቸው፡፡
በባሕር ዳር ደብረ ዓባይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜ መምህር ሐረገወይን በሪሁን ሰላም ለቤተክርስቲያን የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ተልዕኮ ነው ይላሉ፡፡ ሰላም የሚለው ትርጓሜ አንድነት፣ ኅብረት፣ ፍቅር፣ ማስታዋል፣ መረጋጋት፣ መጨመት፣ መረዳት የሚለውን የያዘ ነው፡፡ ፍቅር የሚለው ግን ይወስነዋል ይላሉ መምህሩ፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ድርሻቸው የሰውን ልጅ ሰው ማድረግ ነው፣ ከሰው ግንዛቤ፣ ከሰው መረዳት፣ ከሰብዕና እንዳይወርድ ማነጽ መገንባት፣ ሰውዓዊ ሞራሉን ወደ መላእካዊ ሞራል ማሳደግ እንደሆነም ነግረውኛል፡፡ መላእካዊ ሞራልም ፍቅር፣ ትህትና፣ አንዱ የአንዱን ድካም መሸከም፣ አንዱ አንዱን መርዳት፣ ማገዝ፣ ለኔ የሚያስፈልገው ለባንጀራዬ ያስፈልገዋል፣በአጠቃላይ ሰው ለሆነ ሁሉ ያስፈልገዋል፣ ብሎ እንዲያስብ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
የመላእክት አንዱ የባሕሪያቸው መገለጫ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ስለሚያደርጋቸው ደስታ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ኅብረት እግዚአብሔር ስለሚሰጣቸው ነገሮች ለእነሱ እንደ ተደረገላቸው ያክል መደሰት ነው፡፡ መላእክት ለእነርሱ ሳይሆን ለሰው ልጆች ለተደረገላቸው ደስታና ለተሰጣቸው ደስታ ይደሰታሉ፡፡ ለሰው ልጆች ለሚደረግላቸው ጸጋና በረከት መላእክት ይደሰታሉ፣ የሃይማኖት ተቋማት ድርሻም የሰውን ልጅ ወደ መላእክት ሞራል ከፍ ማድረግ ነው ይላሉ መምህሩ፡፡
ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንም ሃይማኖተኞች ናቸው፡፡ ታዲያ ሃይማኖትና ሃይማኖተኞች ባሉባት ሀገር ሰው ከሰው ግንዛቤ፣ ከሰውነት ማስታዋል ወርዶ አሁን ባለበት ደረጃ ለምን ደረሰ ? በየቀኑ ግጭት እና ሁከት እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? ብለው የሚጠይቁት መምህር ሐረገወይን የሃይማኖት ተቋማት ባለፉት ዓመታት መዳከም ታይቶባቸዋል፣ ወደ ፖለቲካው የመሳብ አዝማሚያም ታይቶባቸው ቆይቷል ነው የሚሉት፡፡ የሃይማኖት መምህራን ሃይማኖቱ ወደማይፈቅደው አካሄድ ተስበው ቆይተዋል፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት አንድ የሃይማኖት መምህር ተናገረ ሲባል ይደመጣል፣ ይሰማል እግዚአብሔር ወርዶ ቃል በቃል እንደተናገረ ያክል ይሰማ ነበር፡፡ አሁን አሁን ይህ እየደበዘዘ መጥቷል ፣ እንዲህ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች የሚያሳዩቸው አላስፈላጊ ድርጊቶች ናቸው ይላሉ፡፡ የድንበር መታለለፍ አለ የሚሉት መምህር ሐረገወይን የሃይማኖት መምህራን ሃይማኖቱ ከሚፈቅደውና ከሚያዝዘው ወሰን ልክ ማለፍ የሃይማኖት አባቶች ቃል እንዳይሰማ አድርጎታል ነው ያሉኝ፡፡
ዓለም አቀፍ ተጽዕኖው ሁሉንም አዋቂ የሆነ ስላልመሰለው፣ የሚነገረው ነገር እንዳይደመጥ አድርጓል፣ አንድ ሰው አዋቂ ነኝ ብሎ ራሱን ካሳመነ የሚነገረውን ነገር እንደተራ ነገር ይቆጥረዋል፣ እሱ ብቻ እንዲናገር ይፈልጋል ይህ በሀገር ላይ ለተፈጠረው ችግር መንስኤ ነው ብለውኛል፡፡ ሁላችንም መናገር እንፈልጋለን፣ አዳምጡ ስንባል ግን ማዳመጥ አንፈልግም፣ መላእካዊ ባሕሪያችንን እንስሳዊ የሆነው ባሕሪያችን አጥቅቶታል፣ ጥሞና፣ መረጋጋት፣ ሁልጊዜ ስለ ሚናገረው ነገር አውቆ መናገር፣ ማስታዋል የመላእካዊ ባሕሪ ድርሻ ነው ይላሉ፡፡
እንስሳዊ ባሕሪ ግልፍተኛነት ይበዛዋል፣እንስሳዊ እና መላእካዊ ባሕሪ ባልተጣጣሙ ጊዜ ሰው ብኩን ይሆናል ነው ያሉኝ፡፡ እንስሳዊ ባሕሪ ሲጎለብት ሰው ማዳመጥ፣ መረጋጋት፣ መረዳት የተሳነው፣ የሚያደርገውን ነገር ለምን እንደሚያደርገው በትክክል የማይረዳ ይሆናል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት አርዓያ መሆን ይገባቸዋልም ብለውኛል፡፡ የሃይማኖት መምህራን የሚያስተምሩትን መኖር፣ በንግግራቸው ብቻ ሳይሆን በድርጊታቸውም ማስተማር አለባቸው ነው ያሉኝ፡፡
ስለ ዘረኝነት መጥፎነት ከሰበኩ፣ ዘረኝነትን የሚጠየፉ መሆን አለባቸው፣ ስለ ገንዘብ ወዳድነት የሚያወሩ ከሆነ ገንዘብ ወዳድ መሆን የለባቸውም፣ ስለ ቂም በቀል አጥፊነት የሚያስተምሩ ከሆነ እነርሱም ይሄን የሚጸየፉ ከሆነ እንደ ትናንት አባቶቻችን ይከበራሉ፡፡ ቃላቸው እግዚአብሔር እንደተናገረው ይደመጣሉ፣ በጦርነት መካከል ቢቆሙ እንኳን አፈሙዝ ይዞራል፣ ጦርነት ይቆማል ሰላምም ይመጣል ብለውኛል፡፡
የሃይማኖት አባቶች ኃላፊነት ሰማያዊ እንደሆነ የነገሩኝ መምህር ሐረገወይን ሰማያዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ምድራዊ ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ መውጣት አለባቸው ነው ያሉኝ፡፡ ሰውን በሥጋው ካልጠበቅከው፣ በነብሱ አትጠብቀውም፣ በሥጋው ሲጠበቅ ጾሞ፣ ጸልዮ፣ ሰጥቶ፣ መጽውቶ፣ ወንድሙን ወዶ፣ አክብሮ ጸጋን ይቀበላል፡፡ ነፍስ ሥራዋን የምትሰራው በሥጋ ነውና ይላሉ፡፡ ሁሉም ሰላምን ይፈልጋት፣ ይጠብቃትም፣ ሁሉም ያለው ከእርሷ ጋር ነውና ነው ያሉት፡፡
አመጻውን ተውት፣ በቀልና ቂመኝነቱንም እርሱት፣ ከሰብዓዊነት ወሰን ላይ ጽኑ፡፡ ያን ጊዜ ምድሯ የተጠማችውን ሰላም ታገኛለች፣ ያን ጊዜ ምድሯ ታርፋለች፣ ሰላምንም ታጣጥማለች ይላሉ መምህሩ፡፡
ዘጋቢ ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!