“ሰላም በሰማይም በምድርም ላሉት ታስፈልጋለች” መምሕር ሐረገወይን በሪሁን

68

ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም በምድር ከሌለች ምድር ትናወጻለች፣ በሰቆቃ ድምጽ ትጨነቃለች፣ በረሃብና በጠኔ ትገረፋለች፣ ሰላም ከሌለች ምድር እረፍት ታጣለች፡፡ ሰላም ከሌለች ሞት ይበረክታል፣ መሳደድና መቅበዝዘብ ይበዛል፡፡

ሰላም ካለች የተናወጸች ምድር ትረጋለች፣ ያለቀሰች ዓይን እንባዋን ታብሳለች፣ የተከዘች ፊት በፈገግታ ትመላለች፡፡ ሰላም ካለች የተቅበዘበዙትን ታረጋለች፣ ለምድር እረፍትና ተድላን ታጎናጽፋለች፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ሰላምን አብዝታ ትፈልጋለች፣ ትረጋና ትጸና ዘንድ ሰላምን ትሻለች፡፡

በባሕርዳር ሀገረ ስብከት የደብረ ዓባይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍት ትርጓሜ መምህር ሐረገወይን በሪሁን ስለ ሰላም ሲናገሩ ሰላምን ፈልጋት፣ ፈልገህም አግኛት፣ ካገኛሃትም በኋላ በእርሷ ለዘላላም ጸንተህ ኑር እንደተባለ ሰላም ዋጋ አይወጣለትም፣ በዋጋ አይለካም፣ በዋጋም አይመዘንም፣ ሰላም ከዋጋ በላይ ነው ይላሉ፡፡

ሰላም፣ የሰው ልጅ እና ጊዜ በምድር ላይ ምንም አይነት ዋጋ አይሠራላቸውም የሚሉት መምሕር ሐረገወይን ዋጋቸው የሰውን ልጅ ሕያው ማድረግ ሕይወቱን መጠበቅ ካልሆነ በቀር ለሰው ልጅ ሕይወት፣ ለጊዜና ለሰላም የምትከፍለው ዋጋ የለም፣ እነዚህ ከዋጋ በላይ ናቸው ይሏቸዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ጸሎት ሰላም ነው፣ ሀገርና ሕዝብ ሰላም እንዲሆን ትጸልያለች፡፡ ሥራዎች እንዲባረኩ ትጸልያለች፣ ስለ ሚፈስሱ አፍላጋት፣ ስለ ሚዘንበው ዝናብ፣ ዝናቡ ስለሚሰጠው አዝርዒት ሁሉ ትጸልያለች፣ ከሁሉ አስቀድማ ግን ስለ ሰላም ትጸልያለች፣ ሰላምንም ታስቀድማለች፡፡ ሰው ሁሉ መውጣት መግባቱ፣ መነሳት መተኛቱ፣ በሰላም፣ በመረጋጋትና በእረፍት ይሆን ዘንድ አብዝታ ትጽልያለች ነው ያሉኝ፡፡

ስለ ራስህ ጸልይ፣ ሰለ ነገሥታቱና ስለ መኳንንቱ ጸልይ፣ ስለ ሀገር ጸልይ፣ ስለ ሕዝቦቿም ጸልይ፣ በጸሎት የጎበጠው ይቃናል፣ በጸሎት የወደቀው ይነሳል፣ በጸሎት የጨለመው ብርሃን ይሆናል፣ የተጨነቀው ይረጋጋልና፡፡ ሰላም ከሌለ መጾም፣ መጸለይ፣ ሰላም ከሌለ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትና ሕዝብን ማዳን አይቻልም ይላሉ መምህሩ፡፡

አምላክ ወደ ምድር ሰው ሆኖ ሲመጣ ዋናው ዓላማው ሰላም ነው ያሉት መምሕር ሐረገወይን ለምድሯ ከእርሱ ውጭ ሰላምን የሚያመጣ ኃይል አልተገኘም፣ እርሱም ለምድር ሰላምን ይሰጣት ዘንድ የሰላም ባለቤት ራሱ መጣ፡፡ ራሱም ከአዳም እና ከልጆቹ ጋር ሰላምን እና ፍቅርን መሠረተ፡፡ ትሕትናውን፣ ይቅር ባይነቱን፣ አዳኝነቱን እና መሃሪነቱን ሰላም በመስጠት ገለጠ፡፡ ሰውም በአርአያ እግዚአብሔር ተፈጥሯል፣ እግዚአብሔር የሰላም ባለቤት ነው፣ እኛም የእግዚአብሔር ልጆች ነን፣ እርሱ የሰላም ባለቤት ነው ብለን፣ ቂመኞች፣ በቀለኞች፣ አጥፊዎች ከሆን ግን የእግዚአብሔር ልጆች አይደለንም እያለን ነው ብለውኛል፡፡

ለመጾምም ሰላም ያስፈልጋል፣ ለመጸለይም ሰላም ያስፈልጋል፣ ምጽዋት ለመስጠት ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ተረጋግቶ የጸለዬ፣ ተረጋግቶ ምጽዋት ያቀረበ መስዋዕቱ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ይኖረዋል ነው ያሉኝ፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፣ ስላም ለፍጥረት የተሰጠች ናት፣ ሰላም የሰው ልጅ የአዕምሮ፣ የኅሊና፣ የልቡና እረፍት ነው፣ ሰላም የምትባለው በሰማይም በምድርም ላሉት ታስፈልጋለች፡፡ ሰላም ለድንጋዩ፣ ለእንጨቱ፣ ለአዕዋፋት ለሁሉም ታስፈልጋለች፡፡ አዕዋፋት ይራቡ፣ ይዋለዱ፣ ይበዙ ዘንድ ሰላም ታስፈልጋቸዋለች፣ ሰላም ለሰው ልጆች ብቻ አይደለም የምታስፈልገው፣ በሰማይ ላሉ ለመላእክት፣ በምድር ላሉ ለደቂቀ አዳም፣ ለእንስሳቱ፣ ለእንጨቱ ሁሉ ሰላም ታስፈልጋለች፡፡

አራሹ አርሶ እንዲያፍስ፣ ነጋዴው ነግዶ እንዲመለስ፣ ሕዝብ ሁሉ በጎዳናዎች እንዲመላለስ ሰላም ታስፈልጋለች፡፡ ኢትዮጵያ ታላቅ ናት፣ ሕዝቦቿም ታላቆች ናቸው፣ ታላቅነታችን፣ ጀግንነታችንን፣ ደግነታችንን ፣ ሃይማኖታችንን እኛ ሳይሆን ዓለም ሲናገር ኖሯል፡፡ ታዲያ አሁን ይሄ ለምን መጣብን? ሲባል ያለንን ነገር አክብረን ባለመያዛችን ነው፣ ወርቃችንን ጥለን እንቅፋት የሚሆነውን ድንጋይ ይዘን በመቅረታችን ነው ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ አለመታመማን፣ አለመግባባት ከተጀመረ ቆይቷልም ነው ያሉኝ፡፡ አባቶቻችን አዕምሯቸው ብሩህ፣ መንፈሰ ጠንካሮች፣ ጠቢባን ነበሩ የሚሉት መምሕር ሐረገወይን በስርዓተ መንግሥት፣ በሥነ ሕዝብ የመጀመሪያዎች ነን ብለን፣ ትናንት የታላቅነት፣ የጀግንነት መገለጫዎች አሉን እያለን ዛሬስ ይሄ ሁሉ የት ሄደ? ሲባል በአዕምሯችን አላመንም ማለት ነው ብለውኛል፡፡ የነበረውን ታሪክ ለማምጣት ሙያና እውቀት ላይ የተመሠረተ ሥራ ያስፈልጋል፣ የአባቶች መሠረት እንደመነሻ ይሆናንልም ብለዋል፡፡

ሀገር የሚፈርሰው የሀገር ሽማግሌ የጠፋ ጊዜ እንደሆነም ነግረውኛል፡፡ የሀገር ሽማግሌ የተቀደደ ሀገር ይሰፋል፣ የሽምግልና ጥበብ፣ የሽምግልና ብልሃትና ግርማ ያላቸው አባቶች ለሀገር ሰላም ዋና ተዋናይ መሆን ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ሽማግሌዎች ምንድን ነው የጎደለን? ምንስ ነው ያጣናው? መሪዎች ለምን ሕዝብን አንድ አድርጎ መምራት ተሳናቸው? አንተም ተው አንተም ተው የሚበጀው ይሄ ነው ብለው ነገሮችን ማጥበብ አለባቸው ብለውኛል፡፡

የሀገራቸውን ታሪክ፣ እሴትና ትውፊት ጥንቅቅ አድርገው የሚያውቁ ሰዎች ሕዝብን ወደ ፍቅር መንገድ መውሰድ ይገባቸዋል፣ ትናንት እኔ ልሙትልህ፣ አንተ ኑር ሲባልባት በነበረች ሀገር ዛሬ እኔ ልኑርበት አንተ ውጣልኝ ወደ ማለት ደርሰናልና፡፡ ሽማግሌ የጠፋባት፣ ሽማግሌም የማይከበርባት ሀገር ጠፊ ናት ነው ያሉት፡፡

ሁላችንም ተናጋሪዎች አንሁን፣ አዳማጮችም እንሁን ነው ያሉኝ፡፡ “ምክር ከሌለ ዘንድ የታሰበው ሁሉ ሳያሳካ ይቀራል” እንደ ተባለ በችግሮች ላይ ዱላ ከመማዘዝ መነጋገር፣ መመካከር ይበጃል ይላሉ፡፡ ሕዝብ እና ሀገር እያለ መነጋገር ይበጃል፣ ሕዝብና ሀገር ከጠፋ በኋላ የሚያነጋገር ጉዳይም፣ መነጋገሪ ሥፍራም ይታጣል፣ ያለንን ከማጣታችን አስቀድሞ እንነጋገር ነው ያሉት፡፡

ማሰብ፣ ማንሰላሰል፣ መመዘን ካልቻልን ከወራጅ ውኃ በምን እንለያለን የሚሉት መምህር ሐረገወይን ወራጅ ውኃ ሰዎች በሚያዝዙት ይጓዛል፣ ወደ ፈለጉበትም መንገድ ይመሩታል፣ ሰው ግን ወደ መሩት አይሂድ ለምን ብሎ ይጠይቅ፣ ያመዛዝን ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ጦርነት ከቆመ ዓመት አልሆነውም፣ አመት ሳይሞላ ወደ ሌላ ጦርነት ውስጥ መግባት ለምን አስፈለገ፣ ካለፈው ጦርነት ያተረፍነው ትፍር ነበረ ወይ? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ንብረት ከማውደም፣ አካል ከማጉደል፣ ከመገዳደል የዘለለ መልካም ሃሳም ማሰብ ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ጠላቶቻችን የሚፈልጉት እንድንበተን እና እንድናልቅ ከሆነ ስለምን የጠላቶቻችን ስራ አስቀድመን በእኛው ላይ እናደርገዋለንም ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ሁሉ ቆም ብሎ ማሰብ አለበት ያሉት መምሕር ሐረገወይን ተገፍተናል ወይ አዎ ተገፍተናል፣ ከፍቶናል ወይ አዎ ከፍቶናል፤ ነገር ግን ሰላምን በማሳጣት ነው ወይ ይሄን ችግር የምናስውግደው ብለን ማሰብ አለብን፡፡ ሰላም ሲጠፋ የአዕምሮ መታወክ፣ የልቡና ሁከት ይመጣል፣ ሰው ደግሞ ልቡናው ከታወከ ምንም ማድረግ አይችልም ነው የሚሉት፡፡ አዕምሮው ሲታወክ ሰው ብሶተኛ ይሆናል፣ ብሶተኛ ደግሞ የመጨረሻው ጸብ ነው፣ ከጸብ አስቀድሞ የምናሽንፍባቸው መንገዶች አሉ ብለዋል፡፡

መሪዎች አስቀድመው ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን መቆጣጠርና ለችግሮች እልባት መስጠት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

መሪ ማለት ከጥቃት የሚከላከል፣ ሕዝብን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ነውም ብለዋል፡፡ መንግሥት እንዲረጋ ሕዝብ መረጋጋት አለበት፣ ሕዝብ ካልተረጋጋ መንግሥት አይረጋም፣ መንግሥት ካረጋ ሀገር ትታመሳለች ነው ያሉት፡፡ ተባብሮ የጋራ ሀገር ማቆምና ማጽናት ይገባልም ብለዋል መምህር ሐረገወይን፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላምን አስፋፉ፣ ሰላምን በመካከላችሁ ስበኩ” ሼህ አብዱረህማን ሱልጣን
Next article“ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት በመሰረታዊ ምርቶችና አቅርቦቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ በኑሯችን ላይ ጫና ተፈጥሮብናል” የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች