‹‹‹ሽፍታ እየቀለባችሁ ስለሆነ ልትጠየቁ ነው› ብለው ነው የወሰዱን፡፡›› ከዕገታ ያመለጠው ታዳጊ

408

‹‹ድርጊቱ እየተፈጸመ ያለው ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል ይመስላል፡፡›› ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አሰምሬ

‹‹ማሩ ፈንታሁን እባላለሁ፤ በገደል ወድቄ ነው ሕይወቴን ማትረፍ የቻልኩት›› ብሏል ከአጋቾች ግድያ በተአምር የተረፈው ታዳጊ፡፡ ማሩ ለአብመድ እንደተናገረው ጀምበር ጎነበ፣ እያያው አዳነ እና እያያው ፈንታሁን ከሚባሉ ጓደኞቹ ጋር በመሆን በጠገዴ ወረዳ ማይዳራ ወንዝ ለመታጠብ በወረዱበት ነበር በአጋቾቹ እጅ የገቡት፡፡ ‹‹ሽፍታ እየቀለባችሁ ስለሆነ ልትጠየቁ ነው›› ብለው ወንዙን አሻግረው ወደ ጫካ እንደወሰዷቸው የተናገረው ታዳጊው ለበርካታ ቀናት አግተዋቸው እንደሰነበቱ ተናግሯል፡፡

ከማይዳራ ወንዝ ኮርኮራ ወደሚባል ቦታ እንደወሰዷቸውና አግተው እንዳቆዩዋቸውም ተናግሯል፡፡ ‹‹እኛን ከማይዳራ ሌሎች አራት ልጆችን ደግሞ ከወንዙ ማዶ ያዙን፡፡ ከዚያ ለቤተሰቦቻችን ስልክ ደውለው ብር ክፈሉ አሉ፡፡ ቤተሰብ ደግሞ ብር እያፈላለጉ መሆናቸውን ነገሩን፡፡ ቀን ቀን ሲያንቀሳቅሱን በገመድ ያስሩናል፤ ስንቀመጥ ደግሞ በሰንሰለት እንታሰራለን፡፡ ቤተሰቦቻችን ብር ካላመጡ እንደሚገድሉን ይነግሩናል፡፡ እሑድ ዕለት የእኔ ወንድም ብር አመጣለሁ ሲል ‹ሄደው እንዳይናገሩ ልጆቹን ገድለን ብሩን እንወስዳን› አሉ፡፡ ከዚያ ሁለት ሁለት እያደረጉ ከነበርንበት ዘወር እያደረጉ መግደል ጀመሩ፡፡ ያን ጊዜ የታሰርንበትን ገመድ በጥሼ በገደሉ ዘልዬ ወረድኩና በተአምር አመለጥኩ፡፡ ከእኔ ጋር ታስሮ የነበረው ግን ለማምለጥ ሲሞክር በጥይት ተመትቶ ሞተ›› ብሏል፡፡

አጋቾቹ በቁጥር አምስት መሆናቸውንና አራቱ የታጠቁ አንዱ ደግሞ ጀሌ (ያልታጠቀ) መሆኑን ታዳጊው ተናግሯል፡፡ አጋቾቹ አንደኛው ወደ 60 ዓመት የሚጠጋ ዕድሜ ያለው እንደሚመስለውና አራቱ ግን ከ20 እስከ 30 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል የሚገመቱ የማያውቃቸው እንደሆኑም ተናግሯል፡፡
‹‹አጋቾቹ ሦስቱ ሁለት እግር ክላሽ እና አንዱ ቋሚ ክላሽ ታጥቀዋል፡፡ ስልክ ቻርጅ የሚያደርጉት በሶላር ነው፤ ያሰነበቱንም ጓደኞቼን ከገደሉበት ኮርኮራ ከተባለው ቦታ ነው፡፡ ከዚያው አካባቢ ከላው መንደር ሄደው እንጀራ ያመጣሉ፤ ደውለው አዝዘው ነው ምግቡን የሚያሠሩት፡፡ እንጀራ እንኳ ባያገኙ ዱቄት አምጥተው ገንፎ ይሠራሉ፡፡ የሚነጋገሯቸውን ሰዎች በስም አይጠሩም እንጅ በስልክ በተደጋጋሚ ያወራሉ፡፡ የሚያስተኙን ከመካከል አድርገው ነው፤ በዚህ የተነሳ ለማምለጥም እነሱን ለመግጠምም ከባድ ነበር›› ብሏል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ምሁራዊ ትንታኔ እንዲሰጡን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ፍልስፍና ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አሰምሬን ጠይቀናል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደተናገሩት ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ መደራደሪያ የማድረግ ድርጊቶች በተለያዩ ሀገራት ይፈጸማሉ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ እየታዬ ያለው ግን ከተለመደው ወጣ ያለ እና የመንግሥት ቸልተኝነት ያስከተለው ነው፡፡ ‹‹የኛ አገሩን እገታ የተለዬ የሚያደረገው አንድም በመንግሥት ቸልተኝነት የሚመነጭ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሌሎች ሀገራት ዕገታ የሚፈጸመው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ሲቀሩ በሀብታሞች ላይ የሚፈጠር ድርጊት ነው፤ በኛ ሀገር ግን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ እረኞችን ጭምር ነው እያገቱ ያሉት፡፡ ይህ ድርጊቱን የበለጠ ነውረኛና የሕግ የበላይነት መሸርሸር የወለደው መሆኑን አመላካች ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹ድርጊቱ እየተፈጸመ ያለው ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል ይመስላል፤ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ አለመቻሉን ለማሳዬት ያለመ ነው የሚመስለው፡፡ ድርጊቱ እየተፈፀመ ያለው የፖለቲካ ጥያቄ ባለበት አካባቢ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ጥርጣሬውን ያጎላዋል›› ብለዋል፡፡ የቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ያልተፈታበት፤ የወልቃይትና አካባቢው የማንነት ጥያቄ ያለበት አካባቢ ላይ ድርጊቱ እየተፈጸመ መሆኑን በማንሳት ከእገታው ጀርባ የፖለቲካ ቁማር እንዳለበት አመላካች እንደሆነም ነው ምሁሩ ያመላከተቱ፡፡

የጎንደር አካባቢ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስበት ላይ የሚፈጥረውን ጫና ግምት ውስጥ በማስገባት እና ያንን አካባቢ በማወክ መንግሥትን ደካማ እንደሆነ ለማሳዬት፤ በዚህም ተፅዕኖ ውስጥ ለመጣል የሚጥሩ ኃይሎች እጅ ሊኖርበት እንደሚችልም መገመት እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

ከፖለቲካ አሻጥር ባለፈ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አነሳሽ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ ሀብት ለማካበት የሚደረግ ተራ የሽፍታነት ተግባር የመሆን ዕድል እንደሚኖረው ነው ያመላከቱት፡፡ ነገር ግን የሁሉም ማጠንጠኛ መንግሥት ለሕግ መከበር ትኩረት አለመስጠቱ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ችግሩን መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት ደንታ ቢስ መሆኑ ያመጣው ነው፡፡ በዓለምም በኢትዮጵያም ታይቶ የማይታወቅ የሕግ የበላይነት እጦት እየተስተዋለ ነው፡፡ ስለሆነም የክልልና የፌዴራል መንግሥታት ቅድሚያ ሰጥተው ለሕግ የበላይነት መከበርና ፍትሕ መስፈን መሥራት አለባቸው፡፡ ድርጊቱ የፀጥታ ተቋማትን መዳከም የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት›› ብለዋል፡፡

ወንጀል መሥራት በሕግም በሞራልም የማያስጠይቅና የተለመደ እየሆነ እንደመጣ ያመለከቱት ምሁሩ ‹‹ድርጊቱም ምልክቱም በጣም አደገኛ ነው፤ ምልክቱ የመንግሥትና የሀገር መውደቅን ሁኔታ የሚጠቁም አደገኛ ደወል ነው፡፡ ድርጊቱ በፍጥነት እየጨመረ ስለመጣ የተደራጁ ወንጀለኞች እየበዙ ነው፤ መሠረት ይዟል፤ ግን ሥር ሳይሰድድ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይገባል›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የድርጊቱን አደገኛነት በማጤን የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በፍጥነትና በተቀናጀ አግባብ የሕግ የበላይነትን ወደማስከበር እንዲገቡም ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አሰምሬ መክረዋል፡፡ ሰዎች በሂደት ወንጀልን እየተለማመዱ መሆኑን በማመልከትም የተደራጁ ወንጀለኛ ቡድኖች ሳይበራከቱ መንግሥት መፍትሔ እንዲያበጅ ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

Previous articleከሶማሌና አፋር ክልሎች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ነገ በአዳማ ምክክር ሊያደርጉ ነው፡፡
Next articleየተካረረ የጽንፍ አመለካከት ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ብሔራዊ እርቅ ሳያካሂዱ ወደ ምርጫ መግባት ተገቢ አለመሆኑን ዛሬ ጥምረት የፈጠሩ ፓርቲዎች አሳሰቡ፡፡