“ሰላምን አስፋፉ፣ ሰላምን በመካከላችሁ ስበኩ” ሼህ አብዱረህማን ሱልጣን

62
Made with LogoLicious Add Your Logo App

ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላምን በምድር ሁሉ ዘርጓት፣ ሰላምን ጠብቋት፣ አስጠብቋት፡፡ ሰላም ምድርን ትግዛት፣ ሰላም ምድርን ታጽናት፤ ሰላም ምድርን ታላብሳት፡፡ ሰላም በጠፋች ጊዜ እናት አብዝታ ታለቅሳለች፣ ሰላም በጠፋች ጊዜ ምድር በመከራ ችንካር ትወጠራለች፣ በጦር ትወጋለች፣ በደም ቦይ ትጥለቀለቃለች፡፡

ሰላም በጠፋች ጊዜ ደጋጎች ይሞታሉ፣ ሰላም በጠፋች ጊዜ ሕጻናት ያለቅሳሉ፣ አሳዳጊዎቻቸውን ይነጠቃሉ፣ ሰላም በጠፋች ጊዜ አረጋውያን ያለ ጧሪ ቀባሪ ይቀራሉ፣ ሰላም በጠፋች ጊዜ ጎዳናዎች ሰው ይራባሉ፣ ሰላም በጠፋች ጊዜ ከተሞች ይፈርሳሉ፣ ሰላም በጠፋች ጊዜ ሁሉም ይጠፋል፡፡ ሰላም ባለች ጊዜ ሁሉም ይኖራል፡፡

ሰላም የሁሉም መሠረት ናትና መሠረቷን አጽኗት፣ ሰላም የሁሉ መንገድ ናትና ጠብቋት፤ እርሷ ካለች ደስታ አለች፣ እርሷ ካለች ተድላ ትቀርባለች፣ ሰላም ካለች ምድር ትረጋለች፡፡ ኢትዮጵያ ሙሉ ሰላሟን አጥታለች፣ ሙሉ ሰላሟንም ታገኝ ዘንድ አብዝታ ትደክማለች፡፡ ሙሉ ሰላሟ ይመለስ ዘንድ ልጆቿን አብዝታ ትፈልጋለች፡፡

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼህ አብዱረህማን ሱልጣን ግብረ ግብነት ሲሞላ ሰው ከመጥፎነት ይልቅ ወደ መልካምነት ይሄዳል ይላሉ፡፡

ሼህ አብዱረህማን ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት፣ ሕዝቦቿም ሃይማኖተኞች ናቸው፣ ነገር ግን ሃይማኖቱ የሚለውን ይተገብሩታል ወይ? የሚለው በዚህ ዘመን መታየት ያለበት ጉዳይ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ የሃይማኖት አባቶች የሚያስተምሩት ሕዝብ መንፈሳዊነትን ተላብሷል ወይ የሚለውን ማወቅ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ እውቀትና መንፈሳዊነትን ተላብሶ መተግበር እንደሚለያዩም ነግረውኛል፡፡

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ የሃይማኖት አባቶች ስለ ሰላም በሰፊው መሥራት ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡ ለአማኞቻቸው ሰፊ ግንዛቤ በመስጠት ሃይማኖቱን እንዲኖሩት፣ ሰላምን እንዲኖሩት፣ መንፈሳዊነትን እንዲተገብሩት ማድረግ አለባቸው ይላሉ፡፡

አንድ ልጅ ከልጅነቱ ጀምሮ በምግባር መታነጽ አለበት የሚሉት ሼህ አብዱረህማን ስለ ሃይማኖቱ እየተማረ ማደግና ስለ ሰላም አስፈላጊነት እየተማረ ማደግ አለበት ነው የሚሉት፡፡ “ነብሴ በእጁ በሆነች በአላህ እምላለሁ፣ ሳታምኑ ጀነት አትገቡም” እንዳሉ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እስካልተዋደዳችሁ ድረስ ጀነትን አታገኙም፡፡ ስትዋደዱ፣ አማኝ ትሆናለችሁ፣ አማኝ ስትሆኑ ደግሞ ጀነትን ታገኛላችሁ፣ ጀነትን እንድታገኙ ሰላምን አስፋፉ፣ ሰላምን በመካከላችሁ ስበኩ፤ ሰላምን በመካከላችሁ ስታስፋፉ ትዋደዳላችሁ፣ ስትዋደዱ ታምናላችሁ፣ ስታምኑ ደግሞ ጀነት ትገባላችሁ ብለዋል ነው ያሉት፡፡

ሼህ አብዱረህማን ሰላምን ማስፋት፣ ሰላምን መስበክ ሁሉን ያሰጣል፣ መልካሙንም ያስገኛል ብለዋል፡፡

ከጦርነት ትርፍ የለም፣ ከጦርነት ውድመት፣ ከጦርነት የማኅበረሰብ ቀውስ እንጂ ሌላ ትርፍ የለም ነው ያሉት፡፡ ሰላምን ማውረድ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር ማብረድ እና ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ የሃይማኖት አባቶች ድርሻ ላቅ ያለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ሙስሊሙም ይሁን ክርስቲያኑ ከሃይማኖቱ አስተምህሮ፣ ከሃይማኖት አባቶቹ ተግሳጽና ምክር መውጣት የለበትምም ብለዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች ሰላምን ለማስፈን ከልብ፣ በቆራጥነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ሼህ አብዱረህማን በጦርነት የሚደርሰውን ጉዳት አይተነዋል፣ በግጭት የሚፈጠረውን ቀውስ ተመልክተነዋል፣ ብቸኛ አማራጫችን ወደ ሰላም መምጣት ነው ይላሉ፡፡

ሕዝቡን በማረጋጋት ሰላም ሰፍኖ ሰላማዊ ሕይወት እንዲቀጥል መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች ዘላቂ ሰላም በሀገር ላይ እንዲመጣ የማድረግ አቅም እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሃይማኖት አባቶች ቆራጥ መሆን አለባቸው፣ አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል መቻልም አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ለሕዝባችን ስንል መስዋዕትነት ከፍለን ዘላቂ ሰላምን ማጽናት ይገባናልም ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ሁሉ ከጦርነት የሚገኝ ነገር እንደሌለ ተረድቶ፣ ለሰላም አበርክቶውን ማሳረፍ ይገባዋል የሃይማኖት አባቶችን መቀበል፣ መክራቸውን መስማት እና ወደ ሰላም መጓዝ አለበት ነው ያሉት፡፡ የሃይማኖት አባቶች ሰሚ ሲያገኙ፣ ሁሉም ለሰላም ሲነሳ ሀገር ሰላም ትሆናለች፣ ሕዝብም ከሰላም ይጠቀማል ነው የሚሉት፡፡

ጦርነት የሚጎዳውን ማኅበረሰብ የሚታደገው ሰላም ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ሼህ አብዱረህማን ሁሉም ለሰላም እጅ ሰጥቶ ለሰላም ተገዢ መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሰላም ውጭ ምንም አይነት አማራጭ የለንም፣ ለሰላም ኹሉን መንገድ እናሳይ፣ ስለ ሰላም መልካም ያሰበ፣ ስለ ሰላም መንገድ የጠቆመ የአምላክን ትዕዛዝ እንደፈጸመ ይቆጠርለታል ሲሉ ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአማራ ክልል በተከሰተው አለመረጋጋት የግብርና ግብዓት ማጓጓዝ አልተቻለም” የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማሥፋፊያ ባለስልጣን
Next article“ሰላም በሰማይም በምድርም ላሉት ታስፈልጋለች” መምሕር ሐረገወይን በሪሁን