
ባሕር ዳር: ነሃሴ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማር ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ኀላፊ ጌትነት አማረ የተከሰተው ሁከት እና ብጥብጥ ያስከተለውን ጉዳት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በሁከት እና ብጥብጡ የተነሳ ግብዓት በአግባቡ በሚፈለገው ቦታ ማድረስ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር ለአርሶ አደሮች በፍትኃዊነት ግብዓት ሲያሰራጩ መቆየታቸውን ነገር ግን ይህን ዓላማቸውን እንዳያሳኩ በየአካባቢው የተከሰቱ አለመረጋጋቶች ችግር እንደፈጠሩባቸው ተናግረዋል፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያገለግሉ ነገሮች ውስጥ ማዳበሪያ አንዱ ነው የሚሉት አቶ ጌትነት ዘግይቶ ተገዝቶ ዘግይቶ የገባውን ማዳበሪያ ማሰራጨት አልተቻለም ብለዋል፡፡ ኀላፊው ከ17ሺ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለሚመለከተው አካል ሳይደርስ በመንገድ መቅረቱንም ያነሳሉ፡፡ በሰብል ምርት የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ዞኖች እና ወረዳዎች በችግሩ ምክንያት ግብዓት እየደረሳቸው አለመኾኑንም ገልጸው መጋዝን ላይ ያሉ ግብዓቶችን ለማሰራጨትም አለመረጋጋቱ ሳንካ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሕዝብ ሀብት እና ንብረት ናቸው የሚሉት ኀላፊው ማኅበራትን መዝረፍ ሕዝብን መዝረፍ በመሆኑ ማኅበረሰቡ ኅብረት ሥራ ማኅበራትን በመጠበቅ ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አቶ ጌትነት በተለይ ለኢኮኖሚው መሠረት የኾነውን ግብርና በሰላም እጦቱ ሰለባ እንዳይሆን ሰላምን ማስጠበቅ የኹሉም ድርሻ ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!