
ባሕር ዳር: ነሃሴ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በከተማዋ ተከስቶ በነበረው የሰላም መደፍረስ ዙሪያ ከሚሊሻ አባላቱ ጋር ውይይት አካሂዷል።
አስቀድሞም የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ፣በሚፈጠሩ ችግሮችም ጉዳት ሳይደርስ ለሰላም የመፍትሔ አካል ለመኾን ክፍተቶች መታረም አለባቸው ብለዋል የሚሊሻ አባላቱ በነበራቸው የውይይት መድረክ።
ከአመራሩ እስከ ሚሊሻ አባላቱ በአሠራርና መዋቅር፣ በመረጃና ስምሪት የተናበበና ቅንጅታዊ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል። ችግር ሲፈጠር ብቻም ሳይኾን አስቀድሞ ተገቢው መግባባት መፈጠር አለበት የሚሉት አባላቱ “ሚሊሻነት ሀገርና ሕዝብ የምንጠብቅበት ነውና ክብራችን፣ ሞገሳችንም ነው፣ ሁሌም ዝግጁ ነን” ብለዋል። በቀጣይም ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአድማ በታኝ፣ ከፖሊስና ሚሊሻው ጋር ተናቦ መሥራት ይገባል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ለአሚኮ አስተያየታቸውን የሰጡ የሚሊሻ አባል መልካሙ እንየው፤ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ችግር የነበሩ ስህተቶችንና ጉድለቶችን በውይይት አርሞ ለቀጣይ ተልእኮ መዘጋጀት መልካም ነው ብለዋል።የሚሊሻ አባሉ እኔም በበኩሌ የሚሰጠኝን ተልዕኮ ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ ነው ያሉት። ሌላው የሚሊሻ አባል አማረ በረደድ በበኩላቸው በባሕርዳር ከተማ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግርና ግጭት ወደ ሰላም እንዲመለስ በተቻለ መጠን ኀላፊነታችንን ተወጥተናል ብለዋል። ለቀጣይም የሚፈጠሩ ችግሮችን ተናቦ ለመታገል የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ይገባል ነው ያሉት።
ከተማዋ ከነበረባት የጸጥታ ችግር ተላቃ ወደ ሰለሟ ተመልሳለች ያሉት የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የባ/ዳር ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ፤ በከተማ ደረጃ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል። በቀጣይም የከተማዋን ሰላምና የጸጥታ ችግር ማስጠበቅ የሚያስችል የጸጥታ መዋቅር እንዲኖር ለማስቻል ከሚሊሻ አባላቱና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
የከተማዋን ዘላቂ ሰላም ለማረጋጋጥ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ዶክተር ድረስ፤ የሚሊሻ አባላቱ ከሌሎችም የጸጥታ አካላት ጋር ተናበውና ተቀናጅተው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችሉ በውይይት የዳበሩ አደረጃጀቶች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል። ከከተማዋ ማኅበረሰብ ጋርም የውይይት መድረኮች መደረጋቸውን የጠቀሱት ዶክተር ድረስ ሳህሉ ኅብረተሰቡም የሚፈጠሩ ችግሮች በውይይትና በሰላማዊ መንግድ እንዲፈቱ ቀና መኾን እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!