
ባሕር ዳር: ነሃሴ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር በከተማዋ ተከስቶ በነበረው የሰላም መደፍረስ ዙሪያ ከፖሊስ አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር በተከሰተው የሰላም አለመረጋጋት የሰው ሕይወት ማለፉ እና ንብረትም መውደሙ ተገልጿል።
በወቅቱ በፖሊስ አባላቱ የታዩ ጥንካሬዎችና መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች ተነስተዋል።
የፖሊሱን አቅም በአካልም በሥነልቦናም ማጠናከር እና መልሶ ማደራጀት ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ነው የተነሳው።
በቀጣይ ከሌሎች የጸጥታ አባላት ጋር በመቀናጀት የማኅበረሰቡን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
ማኅበረሰቡም ጥያቄዎችን ጉዳት በሚያስከትል መንገድ ሳይኾን በሰለጠነ አግባብ ማቅረብ ባሕል ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
መንግሥትም ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ሊሠጥ ይገባል ነው የተባለው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የባሕር ዳር ኮማንድፖስት አስተባባሪ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር) የፖሊስ አባሉ ለሕዝብ ጥቅምና ለመለዮው ክብር ቅድሚያ ሊሠጥ ይገባል ብለዋል።
የሰላም መደፍረሱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሕገ ወጥ የቤት ግንባታ ሥራን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎች መፈጸማቸውን አንስተዋል።
በቀጣይ ሰላምን በሚያውኩ ጉዳዮች ላይ የፖሊስ አባሉ መረጃን መሠረት ያደረገ ሥራ ላይ እንዲያተኩር ጠይቀዋል።
ከሚሊሻና ሌሎች የጸጥታ አባላት ጋር መቀናጀትና ሕዝባዊ ወይይቶችን ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኀላፊ ኮሚሽነር እንየው ዘውዴ የተፈጠረውን የሰላም አለመረጋጋት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሕገወጥነት መታየቱን አንስተዋል።
አሁን ላይ የተዘረፉ ንብረቶችን የማሥመለስ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ ከማኅበረሰቡ እና ከሌሎች የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
የሰሜን ምዕራብ እዝ ኮማንድ ፖስት ተወካይ ኮሎኔል ሽፈራው ቢሊሶ እንዳሉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት በየትኛውም ቦታና ጊዜ የሚሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም የሚያስችለው የራሱ አሠራር ያለው የሀገር አለኝታ ተቋማም ነው ብለዋል።
አንዳንድ ኀይሎች የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት በሠራዊቱ ላይ በሚያደርጉት የስም ማጥፋት ዘመቻ ማኅበረሰቡ መደናገር እንደሌለበት ገልጸዋል።
ተቋሙ በቀጣይ ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት የማኅበረሰቡን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራም አንስተዋል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!