“አለመረጋጋት እና ግጭት ሲኖር በሰዎች ላይ ከሚፈጥረው ጫና ባለፈ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ሊያሳጣን ይችላል” የሥነልቦና ምሁር

56

ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመሳሪያ ድምጽን እየሰሙ የሚያድጉ ልጆች ለጊዜው በአምሯቸው ላይ ከሚፈጥረው ጭንቀት በዘለለ ግርግሩን እና የሰላም እጦቱን የሚለማመዱ፣ ለሰው የማይራሩ እና የጭካኔ ሥነ ልቦናን የተላበሰ ትውልድ ሊፈጥር የሚችልበት እድል ሰፊ ነው ይላሉ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የልጅነት እንክብካቤ ትምህርት ክፍል ኀላፊ ዶክተር እባቡሽ ይርዳው፡፡

ዶክተር እባቡሽ እንደሚሉት ሰዎች በሠለጠነ መንገድ ጉዳያቸውን በምክክር መፍታት እየቻሉ ወደ ግጭት የሚያመሩ ከኾነ ለትውልዱ የሚፈጥረው ችግር ዘርፈ ብዙ እና ዘመናት ተሻጋሪ ሊኾን እንደሚችል ነው ያስገነዘቡት፡፡

በተለይም አለመረጋጋት ሲኖር ልጆችም ይኹኑ ማኅበረሰቡ ከመጨነቅ አልፎ በአካባቢው ያለመኖር ፍላጎት፣ ነገሮችን የመርሳትና መሰል ጉዳዮች ጎልተው እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ከመሰረታዊ ፍላጎቶች ቀጥሎ ሰላም እና መረጋጋት ሲኖር ነው ሌሎች ፍላጎቶች የሚኖሩት የሚሉት ዶክተር እባቡሽ የፍቅር እና አብሮ የመኖር እንዲሁም የማክበር፣ የመከበር እና መሰል ሰብዓዊ ጉዳዮች የሚኖሩት ባይ ናቸው፡፡

የሰላም እጦት መማርን ፣ አርቆ ማሰብን እና ሌሎችንም ጉዳዮች ሊገታ እንደሚችልም መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ሰላምን ማጣት ሰብዕናን እንደሚያዛባ እና ዓላማ የሌለው ትውልድ እንደሚፈጥርም ምሁሩ አብራርተዋል፡፡

እንደዚህ ከኾነ ደግሞ በሌላው ዓለም እንደሚታየው በሰው ልጆች የሚጨክን ትውልድ ሊፈጥር የሚችልበት እድሉ ሰፊ በመኾኑ ሁሉም ዜጋ በያገባኛል ስሜት ለሰላም መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።

ሰላምን ማጣት በተለይ በልጆች ትምህርት አቀባበል ላይ ጉዳቱ ሰፊ እንደሚኾንም ነው ያስረዱት፡፡

ልጆች ነጻ ሲኾኑ፣ ደስተኛ ሲኾኑ እና የተረጋጋ የመማሪያ አካባቢ ሲፈጠርላቸው ነው የተሻለ የትምህርት አቀባበል እና ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚኾኑት ይላሉ፡፡

በቀጣይ ወርም ትምህርት የሚጀመርበት ወቅት በመኾኑ ለዚህ የሚመች አካባቢ ካልተፈጠረ በትውልድ ቅብብሎሹ ላይ ሳንካ እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል፡፡

አሁን ላይ ልጆች እየሰሙ ያሉት ያለመረጋጋት ኹኔታ ስለትምህርት እንዲያስቡ ከማድረግ ይልቅ አዕምሯቸውን የሚያዛባ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

ልጆች መቸ ነው የሚደመጡት የሚሉት ዶክተር እባቡሽ ልጆች እንዳዋቂዎች አደባባይ ቢወጡ የሚያስሙት መልእክት ሰላማዊ አካባቢን ፍጠሩልን የሚል እንደሚኾን ከሚያሳዩት እና ከሚናገሩት ቃላት መገንዘብ ይቻላል ይላሉ፡፡

የትኛውም ዓለም ላይ ያለ ያደገ ማኅበረሰብ ልጆችን አዳምጦ እና ከሁከት እና ግርግር ርቀው እንዲያድጉ በማድረግ እንጂ የሀገር ሀብቱ የሚበላለጥ እንዳልኾነም ገልጸዋል፡፡ ትውልዱ ጭንቅላት ላይ የሚሠራው ሥራ ሀገራትን እንደሚያለማም ነው ያብራሩት፡፡

አሁን ላይ በተፈጠረው ችግር ዋና ተጎጅዎች ሕፃናት፣ እናቶች እና አቅመ ደካሞች በመኾናቸው ሁሉም እነዚህን አካላት ታሳቢ አድርጎ ከግጭት ይልቅ ወደ ሰላማዊ ምክክር መምጣት አለባቸው ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት እና በመመካከር በመፍታት ትኩረት በሚሹ የኀብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ ይገባል” የአማራ ክልል ሴቶች ፣ ህጻናትና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ
Next articleኅብረተሰቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ፖሊስ ጠየቀ።