
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም እጦት ሁሉንም የኀብረተሰብ ክፍል ይፈትናል፤ ይጎዳልም፡፡ ሰላም ከሌለ ማንኛውም የኀብረተሰብ ክፍል በሰላም ወጥቶ መግባት ፣ መሥራት እና የዕለት ከዕለት ተግባራትን መከወን አይችልም፡፡ ለሰብዓዊም ኾነ ቁሳዊ ጉዳትም ያጋልጣል፡፡
በአማራ ክልል ሴቶች ፣ ህጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ወይዘሮ ምጥን ብርሃኑ እንደሚሉት የሰላም እጦት ሁሉንም የኀብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ ቢኾንም በተለይ ትኩረት የሚሹ የኀብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ህጻናት፣ አረጋውያን፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች ይበልጥ ለከፋ አደጋ ተጋላጭ ይኾናሉ፡፡ በጦርነት እና በግጭት ወቅት የሚከሰቱ የህይወት ማጣት፣ የቁሳቁስ መውደም እና የሥነ ልቦና ችግሮች ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል በጋራ የሚጋሩት ይሁን እንጂ በህጻናት፣ አረጋውያን፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ለአብነት በሚፈጠር የሰላም እጦት ምክንያት ሴቶች ለጤና ፣ለኢኮኖሚያዊ ፣ ማኀበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫናዎች ተጋላጭ ናቸው ያሉት ወይዘሮ ምጥን የሰላም እጦት ባለበት አካባቢ የሚኖሩ ነብሰ ጡር እናቶች ተገቢውን ቅድመ እና ድኀረ የህክምና ክትትል ለማድረግ እና የተመጣጠነ ምግብ ለማግኘት አይችሉም፡፡ ይህም በእናትየዋ ላይ የጤና፣ የሥነ ልቦና እና አካላዊ ቀውስ እንዲሁም በጽንሱ ላይ የጤና ችግር ያስከትላል፡፡
በተለይ በመውለጃቸው ወቅት የሚገኙ እናቶች በቤት እንዲወልዱ፣ በቤታቸው መኾን ካልቻሉ ደግሞ በከፋ እና ምቹ ባልኾኑ ቦታዎች እንዲወልዱ እንደሚገደዱም ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የእናትየዋን እና የህጻኑን ደኀንነት አደጋ ላይ የሚጥል እና ህይወት ለመስጠት ህይወት እስከማጣት ሊያደርስ የሚችል እንደኾነም ወይዘሮ ምጥን አንስተዋል፡፡ ታዲያ ይህ ችግር በእናት እና በልጅ መካከል ብቻ የሚቆም አይደለም የሚሉት ኀላፊዋ ይልቁንም ችግሩ ተሻግሮ ሀገራዊ ችግር ኾኖ ይቀጥላል ባይ ናቸው፡፡ እንደ ሀገር ጤናማ እና አምራች ትውልድ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረትም በእጅጉ ይፈትነዋል ብለዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ምጥን ገለጻ በሰላም እጦት ምክንያት በሚፈጠር መሰደድ እና መፈናቀል ሴቶች እድሜ ሳይገድባቸው ለሥነ ልቦና ፣ ለአካላዊ እና ጾታዎ ጥቃት ይጋለጣሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ግጭቶች ሲከሰቱ ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች ወንዶች በመኾናቸው የህይወት አጋሮቻቸውን በሞት የማጣት አጋጣሚዎች ስለሚኖሩ ቤተሰብ የማስተዳደሩ ጫና ሴቶች ላይ ይወድቃል ብለዋል፡፡
የሰላም እጦት ህጻናትን ለአካል ጉዳት፣ ለሞት እንዲሁም አሳዳጊ እና ወላጅን በሞት የማጣት እና ከወላጅ እና አሳዳጊ የመለያየት ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ተዳምሮ ሀገርን ለማኅበራዊ አና ኢኮኖሚያዊ ቸግሮች ያጋልጣል ነው ያሉት፡፡
አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን በባሕሪያቸው በሰላም ጊዜ እንኳ የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን ለመከወን ልዮ ድጋፍ እና እንክብካቤ የሚሹ የኀብረተሰብ ክፍሎች ናቸው ያሉት ወይዘሮ ምጥን አካል ጉዳተኞች ከጉዳት አልባ ሰው አንጻር ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል እና ለመሸሽ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገርም አብዛኛዎቹ አካል ጉዳተኞች በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ እንደመገኘታቸው በሚፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት በእጅጉ እንደሚፈተኑ አንስተዋል፡፡ በሰላም እጦቱ ምክንያት በሚፈጠሩ የቁሳቁስ እና የድጋፍ መሰበር ምክንያት ጥገና እና ክትትል የማግኘት እድልን ስለሚያጡ ለተወሳሰበ ችግር ይዳረጋሉ ብለዋል፡፡
ሰላም እንዲመጣ ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ድርሻ ቢኖረውም በተለይም እናቶች አርቆ አሳቢ ፣ ሰላም ወዳድ፣ ግጭትን የሚጠላ፣ ችግሮችን በጦርነት ወይም በጉልበት ሳይኾን በውይይት የሚፈታ፣ የሚከባበር እና የሚተሳሰብ ትውልድ የመቅረጽ ቤተሰባዊ ሚናቸውን ተጠቅመው ትውልድ የመቅረጽ ኀላፊነታቸውን አንዲወጡ ወይዘሮ ምጥን አሳስበዋል፡፡
አረጋውያን በኀብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሰላም እንዲሰፍን፣ አንድነት እንዲጠናከር፣ እርስ በርስ የመከባበር እና የመፋቀር እሴቶች እንዲጎለብቱ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ ማኅበረሰባዊ እሴቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ ለሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአጠቃላይ ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍሎች እና የሚመለከታቸው አካላት ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ በመፈለግ ረገድ የመወያየት እና የመመካከር ባሕልን በማዳበር ችግሮችን የመፍታት አቅምን ማጎልበት ይገባቸዋል ፤ ከዚህ ውጭ በኾነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት መሞከር ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ከማስከተል የዘለለ መፍትሔ አያመጣም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፋሲካ ዘለዓለም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!