የተከሰተው አለመረጋጋት ሥራቸውን ባግባቡ እንዳያከናውኑ እክል እንደፈጠረባቸው አገልግሎት ፈላጊዎች ተናገሩ፡፡

38

ባሕር ዳር: ነሃሴ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሚገኙ አብዛኞቹ ከተሞች በተከሰተው አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን ተከትሎ አገልግሎት ሠጪ ተቋማት ወደ ሥራ በመግባት ላይ ናቸው።

በባሕር ዳር ከተማ አሚኮ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች አሁንም ቢሮዎች ተከፍተው ሠራተኞች ይግቡ እንጂ የሚፈልጉትን አገልግሎት እያገኙ አለመኾኑን ተናግረዋል።

ከአገልግሎት ፈላጊዎች መካከል ደግሞ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች እና አዲስ ንግድ ፈቃድ የሚያወጡ አካላት ብዙውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ግብራቸው ተወስኖ ፈቃዳቸውን የሚያሳድሱት ከነሐሴ 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡

ይህን አገልግሎት ለማግኘት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እንደነገሩን በንግድ ሥራ ላይ ተሠማርተው ቤተሠባቸውንም ሀገራቸውንም እያገለገሉ ነው፡፡ ካሁን በፊት የንግድ ፈቃድ የሚታደስ በኦንላይን ነበር ይላሉ፡፡ አሁን በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎት ባለመኖሩ ከአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አዲስ ፈቃድ ለማውጣት እና ለማሳደስ ለቀናት ቢመላለሱም ኢንተርኔት ባለመለቀቁ በአጭር ጊዜ አጠናቅቀው ወደ ሥራቸው መመለስ አለመቻላቸውን ያነሳሉ፡፡ በዚህም ሥራቸው እየተስተጓጎለ መኾኑን ነው ያስረዱት፡፡

በሥራቸው ለሚያስተዳድሯቸው ሠራተኞች ደመወዝ ለመክፈል ሥራ ማቋረጣቸው እንቅፋት ኾኖባቸዋል፡፡ በተጨማሪ የባንክ እዳ ላለበት ሰው አስቸጋሪ መኾኑንም ያነሳሉ፡፡

አስተያየት ሰጪው ተከስቶ በነበረው ብጥብጥ የተገዛ ቁሳቁስ መግባት አለመቻሉም ሌላው ችግር መኾኑን ይገልጻሉ፡፡

ሰላም ከሁሉም ነገር በፊት አስፈላጊ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪው በችግሩ ምክንያት መብራት እና ውኃም በመጥፋቱ አካባቢያቸው ላይ ችግር ተፈጥሮ መቆየቱን ያነሳሉ፡፡ በመኾኑም ሁሉም ሰው ሰላም እንዲመጣ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሠጪ በውክልና ንግድ ፈቃድ ለማስመዝገብ ነው የመጡት፡፡ ኢንተርኔት ባለመኖሩ በሠዓቱ ጨርሰው መሄድ አልቻሉም፡፡ ይሕም ለአላስፈላጊ ወጭ አጋልጧቸዋል፡፡

በሰላሙ ጊዜ ይህ መሰል እንግልት ባለመኖሩ አገልግሎት ፈላጊው ባሉ አማራጮች አገልግሎት ማግኘት እየቻለ ሁሉም ሰው ግዴታ ቢሮ ላይ መጥቶ እንዲመዘገብ ያስገደደው የሰላም እጦቱ መኾኑን ተናግረዋል።

ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ሰው መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ እድሳት ባለሙያው በበኩላቸው በተከሰተው ችግር ቢሮ በመዘጋቱ በርካታ ደንበኞች ለመመዝገብ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ቢሯቸው በርካታ ደንበኞች ያሉት ቢኾንም በኦንላይን ሲሥተናገድ ሥራው ቀላል እና ጊዜ የማይወስድ ነበር፤ አሁን ሁሉም ቢሮ መጥቶ የሚሥተናገድ መኾኑ እና ኢንተርኔት ባለመሥራቱ የሥራ መደራራብ እንደተፈጠረ ያነሳሉ፡፡

ከኢንተርኔት ውጭ የሚሠሩ ሥራዎችን ብቻ እያከናወኑ መኾናቸወን የሚያነሱት ባለሙያው፤ አገልግሎት ፈላጊው የሚፈልገውን ፈጣን አገልግሎት መሥጠት እንዳልተቻለም ገልጸዋል፡፡

አሁን አገልግሎት እየሠጠን አይደለም የሚሉት ባለሙያው ሰላምን መጠበቅ ከሁሉም ቀዳሚ ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የፀጥታ መደፍረስ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል እና ሁሉም ሰላሙን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ተገኝቶ እንደታዘበው በርካታ አገልግሎት ፈላጊዎች ቢኖሩም ኢንተርኔት ባለመኖሩ ጥቂቶች ከሠዓት እንዲመጡ ሲቀጠሩ ቀሪዎቹ ኢንተርኔት እስኪመጣ ሲጠብቁ ተመልክቷል፡፡

ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሸዋሮቢት ከተማ ማኅበረሰብ የጦርነትን ጥፋት ጠንቅቆ ስለሚረዳ ሰላምን አጥብቆ ይሻል” የከተማዋ ነዋሪዎች
Next article“የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት እና በመመካከር በመፍታት ትኩረት በሚሹ የኀብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ ይገባል” የአማራ ክልል ሴቶች ፣ ህጻናትና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ