
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋሮቢት ከተማ ባለፉት ቀናት ተከስቶ ከነበረው ግጭትና አለመረጋጋት ወጥታ በተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደምትገኝ ነዋሪዎች ለአሚኮ ገልጸዋል።
የፀጥታ አካላት ከነዋሪዎች ጋር በመኾን ስለከተማዋ ዘላቂ ሰላም ውይይት እና ምክክር እያደረጉ ስለመኾኑም ተነግሯል። ውይይቱ ዛሬ ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም የተጀመረ ሲኾን በኮማንድ ፖስቱ እገዳ ተጥሎበት የነበረው የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎትም በዛሬው ዕለት ሥራ ጀምሯል።
ከተማዋ የተለመደውን የትራንስፖርት ፍሰት ያለምንም መስተጓጎል እያስተናገደች እንደምትገኝም ነዋሪዎች ተናግረዋል።
እንደ ነዋሪዎች ገለጻ በከተማዋ ውስጥ ባንኮች የተሟላ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶችም ደንበኞቻቸውን እያስተናገዱ ነው። ሱቆች እና ሌሎችም የንግድ ቤቶች ክፍት ኾነው በተለመደው እንቅስቃሴ ውስጥ ስለመኾናቸውም ተገልጿል።
“የሸዋሮቢት ከተማ ማኅበረሰብ የጦርነትን ጥፋት ጠንቅቆ ስለሚረዳ ሰላምን አጥብቆ ይሻል” ያሉት ነዋሪዎቹ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባሕል መዳበር እንዳለበትም መክረዋል።
እንደ ሕዝብ ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች ያሉ ቢኾንም በሰከነ መልኩ ወደ መንግሥት ቀርበው ምላሽ እንዲሰጣቸው ሰላማዊ ትግል ማድረግ እንጅ ወደ ትጥቅ ትግል ማምራት ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው ያመዝናል ነው ያሉት። “ሕዝቡ ስክነትን፤ መንግሥት ደግሞ የሕዝብን ጥያቄ በአግባቡ ተቀብሎ የመመለስ ፍጥነትን መላበስ አለባቸው” ሲሉም ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አሁን ላይ የተመለሰው የሸዋሮቢት ከተማ ሰላም በዘላቂነት እንዲፀና የሁሉንም ነዋሪዎች የተለመደ የጋራ ርብርብ እንደሚፈልግም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!