
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላምን፣ ፍቅርና አንድነትን በእጅጉ ከሚሹ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ነው። የቱሪዝሙ ዘርፍ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከእለት ጉርስ እስከ ሀገር እድገትና ገጽታ ግንባታ ላይ የሚሠሩ አካላት የሚሳተፉበት ነው።
የበርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች ባለጸጋ የኾነው አማራ ክልል ከሀገር ውስጥ ጎብኝዎች እስከ ዓለም ዳርቻ የሚመጡ ጎብኝዎችን በፍቅር በማስተናገድ የረጅም ጊዜ ልምድና ታሪክ አለው። ይሁንና ቀደም ብሎ በኮሮና ወረርሽኝ፣ ቀጥሎም በጦርነት የቱሪዝም ዘርፉ ክፉኛ ሲጎዳ ቆይቷል። አሁን ደግሞ በክልሉ የተከሰተው ወቅታዊ አለመረጋጋት ሌላው አሉታዊ ተጽእኖ ያሣደረ ሁኔታ ነው።
የታሪክ መናገሻዋ ጎንደር ከተማም ጎብኝዎቿን በፍቅር ተቀብላ የማሰተናገዱ፣ የታሪክ ድርሳኗን፣ የባሕል አምባዋን፣ ጥንታዊ አሻራዋን የማስጎበኘቱ ሁነት አሁን ላይ በተፈጠረው ጊዜያዊ የጸጥታ ችግር ተገትቷል።
ጎንደር አሁን ላይ ወደ ቀደመ ሰላሟ እየተመለሰች በመሆኗም አስጎብኝዎች እንገዶቻቸውን ለመቀበል ከመዘጋጀት ባለፈ ወደ ቦታው እንዲመጡ እየሠሩ ነው።
አቶ አበባው ጥላሁን በጎንደር ከተማ የአስጎብኝዎች ማሕበር ሊቀመንበር ናቸው። የተፈጠረው አለመረጋጋት የማህበሩ አባላት መደበኛ ሥራቸውን እንዳይሠሩ እንዳደረጋቸው ነግረውናል። አቶ አበበ እንደሚሉት የቱሪዝም ዘርፍ በቀጥታ ሰላምና ምቹ ሁኔታን በእጅጉ ይፈልጋል፤
ሰላም ሲደፈርስ፣ አለመረጋጋት ሲመጣ እንቅስቃሴ ይገታልና ጉብኝትም የማይታሰብ ነው ብለዋል።
እሳቸውን ጨምሮ አስጎብኝነት ለበርካቶች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ ቤተሰብ የሚመሩበት የሥራ ዘርፍ፣ የእንጀራ ገመዳቸው እንደኾነ የሚናገሩት አቶ አበበ ለዚህም ሰላም ወሳኝ ነው ብለዋል።
የቱሪዝም እንቅስቃሴ መገደብ ለቱሪስቶች የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ፣ በባሕል አልባሳት ግብይት፣ በየደረጀው ያሉ ምግብ ቤቶችን ጨምሮ ሆቴሎች ላይ ሁሉ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳደረ ተናግረዋል።
በከተመዋ የቱሪዝም አስጎብኝው በለጠ ተረፈ እንደተናገረው በክልሉ በየወቅቱ የሚፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በተለይም የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ወደ ክልሉ እንዳይመጡ በማድረግ በኩል ክፉኛ ጉዳት አለው።
አሁን በከተመዋ በታየው አንጻራዊ ሰላም የጎንደርና አካባቢው ጎብኝዎችን እየመጡ ቢኾንም ተቀዛቅዟል፣ በየአቅጣጫው ያለው ስጋት ጎብኝዎች ወደ ከተማዋ እንዳይመጡ አድርጓል ብሏል።
ለቱሪዝም ልማትና እድገት መንግስት ዘላቂ የሰላም ሥራን መሥራት እንደሚገባው ነው የተናገረው።
በሰላም ውጤት የምንተዳደር፤ በሰላም ውጤት በሰላም የምንኖር ሁሉ ለሰላም ዘብ እንቁም ያሉት ደግሞ አቶ አበባው ጥላሁን ናቸው።
ሰላም በፍላጎት ብቻ አይመጣም የሚሉት አቶ አበባው ከሁሉም ወገን ንግግርን ማስቀደም እና ለሰላም በተግባር መሥራት ይገባል ባይናቸው።
ለሰላም ሰላማዊ ውይይትና ንግግር ያስፈልጋል፤ ለዚህም ሁሉም ሰው ኀላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!