
ባሕር ዳር: ነሃሴ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተያዘው የምርት ዘመን 686 ሺህ 376 ሄክታር መሬት በአኩሪ አተርና በሰሊጥ ሰብል እየለማ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ለኢንዱስትሪ ግብዓትና የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኙ ሰብሎች የተሻለ ምርት ለማግኘት ግብ ተይዞ እየተሠራ መሆኑ ቢሮው ገልጿል።
በዚህም በምርት ዘመኑ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኘው የሰሊጥ ሰብል 340 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ በተደረገው የተጠናከረ እንቅስቃሴ 446 ሺህ 263 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ አስታውቀዋል።
ይህም ከዕቅዱ በ106 ሺህ 263 ሄክታር ብልጫ እንዳለው ጠቁመው ቀሪው መሬት በአኩሪ አተር ሰብል የለማ መሆኑን አስረድተዋል።
በአኩሪ አተርና በሰሊጥ ሰብል እየለማ ካለው መሬትም ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በቅርቡ በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር አሁን እየተሻሻለ በመምጣቱ በዕቅድ የተያዘው ምርት እንዲገኝ ለአርሶ አደሩ የሚደረገው የድጋፍና ክትትል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ጌትዬ ገብሩ በበኩላቸው፤ በምርት ዘመኑ 550 ሄክታር መሬት በሰሊጥ፣ በአኩሪ አተርና በማሽላ ሰብል እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአፈር ማዳበሪያ በአግባቡ በመጠቀም የሰብል ልማት ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የዝናብ ስርጭቱ ለልማቱ ተስማሚና ምቹ በመሆኑ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሠራተኞችን በመቅጠር የአረምና የሰብል እንክብካቤ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሁለት ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ሰብል ሸፍነው እያለሙ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የመተማ ወረዳ አርሶ አደር ይመር ሰጠኝ ናቸው።
በዘንድሮው የመኸር ወቅት በአኩሪ አተር ካለሙት መሬት የተሻለ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በሰሊጥና በአኩሪ አተር ከለማው መሬት 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!