በተከሰተው የሰላም መደፍረስ በገቢ አሰባሰቡ ላይ ችግር እንዳጋጠመው የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ፡፡

45

ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮው በ2016 በጀት ዓመት ከ65 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ሥራ ቢገባም በክልሉ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ለመሰብሰብ የታቀደው ገቢ አለመሳካቱን ገልጿል፡፡

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኀላፊ ክብረት ሙሐመድ እንዳሉት ባለፉት ወራት አዲሱን የቁርጥ ግብር ጥናት በማካሄድ ግብር ከፋዩ ግብሩን በተገቢው መንገድ እንዲከፍል ዝግጅት ቢደረግም በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ወደ ተግባር ማስገባት እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

የክልሉን ሕዝብ የመልማት እና የደኅንነት ጥያቄ የሚፈታው ግብርን በወቅቱ እና በተገቢው መንገድ መክፈል ሲቻል ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ግብር ከፋዩ ሰላሙን እያስጠበቀ በወቅቱ ግብር በመክፈል ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ክብረት እንዳሉት ክልሉ ሰላም በነበረበት በ2015 በጀት ዓመት ቢሮው ለመሰብሰብ ካቀደው ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ውስጥ 89 በመቶ ገደማ ማሳካት ችሏል፡፡

ከ2014 በጅት ዓመት ከተሰበሰበው ገቢ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ11 ቢሊዮን ብር እድገት አሳይቷል ይህም የኾነው ክልሉ ሰላማዊ ሁኔታ ስለነበረ እንደኾነ መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ግብር ከፋዮችም ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል የክልሉ ልማት እንዲፋጠን አድርገዋል ብለዋል ምክትል ቢሮ ኀላፊው ፡፡

ቢሮው ከመንግሥት የሥራ ሰዓት ውጭ ጭምር በመሥራት አሁን ላይ በሰላም መደፍረስ ምክንያት ወደ ኋላ የቀረውን አቅዱን ለማሳካት ርብርብ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የክልሉን ሕዝብ የመልማት እና የደኅንነት ጥያቄ ለመፍታት እና የማኅበራዊ አገልግሎት መሥጫ ተቋማትን መደበኛ ሥራ ለማስቀጠል ግብር ከፋዩ የተጣለበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል እና ሰላሙን ነቅቶ በመጠበቅ ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡

ማኅበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላትም ሰላሙን በመጠበቅ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አካባቢው ወደነበረበት ሰላም በመመለሱ የግብርና ሥራችንን በአግባቡ እያከናወን ነው” የፋርጣ ወረዳ አርሶ አደር
Next article“በአማራ ክልል ከ686 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በአኩሪ አተርና በሰሊጥ ሰብል እየለማ ነው” የክልሉ ግብርና ቢሮ