“አካባቢው ወደነበረበት ሰላም በመመለሱ የግብርና ሥራችንን በአግባቡ እያከናወን ነው” የፋርጣ ወረዳ አርሶ አደር

57

ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር የማታ ቢሠጥ የፋርጣ ወረዳ ሳህርና ቅፍጠት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡

ከሰሞኑ በተከሰተው አለመረጋጋት በቀበሌው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል፤ እንስሳት ሞተዋል፤ የእርሻ ማሳዎች ጉዳትን አስተናግደዋል ይላሉ አርሶ አደር የማታ፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም እጦት በመኖሩ የእርሻ ሥራቸው ተቋርጦ መቆየቱንም አርሶ አደሩ ይናገራሉ፡፡

አሁን ላይ ሰላሙ በመመለሱ ወደ እርሻ ሥራቸው ተመልሰው ሰብላቸውን እየተንከባከቡ ነው፡፡

የሰላም እጦት ሁሉም ሥራ ፈትቶ እንዲውል አድርጓል ይላሉ አርሶ አደሩ፡፡

በተፈጠረው የሰላም እጦት የበርካታ አርሶ አደር ልጆች እንደወጡ አልተመለሱም፡፡

አርሶ አደር የማታ በእሳቸው ቀበሌ ተከስቶ የነበረው ሁከት እና ብጥብጥ ቀጣይ ለሚዘሩ ሰብሎችም ኾነ ካሁን በፊት ለተዘሩ ሰብሎች የሚኾን ማዳበሪያ እንዳላገኙ ያነሳሉ፡፡

አርሶ አደሮች በሁለተኛ ዙር በሚጨምሩት ማዳበሪያ ተሥፋ አድርገው የዘሩት በቆሎ አሁን ላይ በሰላም እጦት ምክንያት ማዳበሪያ ማግኘት አልቻልንም ነው ያሉት።

ከጳግሜ 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30/2016 ዓ.ም የሚዘሩ ሰብሎችም ማዳበሪያ ያስፈልጋል የሚሉት አርሶ አደሩ በቀጣዩ ሁለት ሳምንት ወደ ወረዳዋ የማይገባ ከኾነ ክንክና የሚባለውን የገብስ ዓይነት መዝራት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
ከሁከት እና ከብጥብጥ በፊት በወንድማማችነትና በመነጋጋር ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከሑከት የሚገኝ አንዳች ጥቅም የለም፤ ከውይይት ግን መፍትሔ ይመጣል ብለዋል አርሶ አደር የማታ፡፡

ሰላም እንዲመጣ አርሶ አደሩ ከመንግሥት ጋር እየሠራ እንደኾነ የተናገሩት አርሶ አደሩ የግብርናው ሥራ ውጤታማ እንዲኾን ሁሉም ለሰላም ዘብ ይቁም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየለጋምቦ ወረዳ በአሁኑ ወቅት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱ ተገለጸ፡፡
Next articleበተከሰተው የሰላም መደፍረስ በገቢ አሰባሰቡ ላይ ችግር እንዳጋጠመው የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ፡፡