ኩረጃን ለማስቀረት የአማራ ክልል መምህራን ማኅበር፣ የተማሪ ወላጆች ማኅበርና የክልሉ ትምህርት ቢሮ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን አስታወቁ፡፡

342

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 20/2012ዓ.ም (አብመድ) ኩረጃ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በትምህርት ዘርፉ ላይ የተጋረጠ አደጋ ሆኖ ተስተውሏል፡፡ በተለይም ደግሞ በሀገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ ተደጋጋሚ ዋጋ ማስከፈሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ የአንዳንድ ትምህርት ቤቶች መምህራን በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ኩረጃን በግልጽ ያበረታቱ እንደነበር የአማራ ክልል የተማሪ ወላጆች ማኅበር ፕሬዝዳንት አዱኛው እሸቴ እና የአማራ ክልል መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት እናውጋው ደርሰህ ተናግረዋል፡፡ ኩረጃን የሚያበረታቱ የተማሪ ወላጆች እና ‹የትምህርት ቤታችን ገጽታ እንዳይበላሽ› በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ኩረጃ ሲከናወን በዝምታ የሚያልፉ መምህራን መኖራቸው በግምገማ መረጋገጡን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙላው አበበ ናቸው፡፡

ኩረጃን ለመከላከል ለተከታታይ ዓመታት ቢሠራም ውጤታማ ሊሆን አለመቻሉን ነው አቶ ሙላው የተናገሩት፡፡ በኩረጃ ሂደት ተሳትፎ ያላቸውን ተማሪዎች፣ ፈታኞች፣ ሱፐርቫይዘሮችና ጣቢያ ኃላፊዎች ተጠያቂ የሚያደርግ የአፈታተን እና አስተዳደር መመሪያ ቢኖርም ትግበራው ክፍተት እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

አቶ እናውጋው ደርሰህ እንዳሉት ከጊዜ ወደ ጊዜ በአሳሳቢ ደረጃ እየተስፋፋ ላለው ኩረጃ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሔ ካልተፈለገለት ኢትዮጵያን ለውድቀት ያጋልጣል፡፡ ሀገሪቱ ብቁ የሰው ኃይል እንዳታዘጋጅ በማድረግ ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ እንዳትሆን አቅም እንደሚያሳጣትም ተናግረዋል፡፡ ይህንን ሐሳብ የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊውም ሆነ የተማሪ ወላጆች ማኅበር አጠናክረውታል፡፡

መንግሥት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች ለትምህርት የሰጡት ትኩረት አናሳ መሆን፣ የፈተና ሥርዓትን አለማክበር፤ የመምህራን ተማሪ የማብቃት አቅም አናሳ መሆን እና የተማሪዎች በራስ የመተማመን አቅም ማጣት ለኩረጃ መስፋፋት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች በፍጥነትና በዘላቂነት ለመፍታትም በጥምረት ኩረጃን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እየሠሩ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ሕጻናት በሥነ-ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ፣ በራስ የመተማመን አቅማቸው እንዲጎለብት መምህራን በትኩረት እንዲሠሩ ማድረግ፣ በፈተና ወቅት ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ፣ በቂ መፈተኛ ክፍሎች ማዘጋጀት፣ የተማሪዎችን ግንዛቤ ማሳደግ እና የወላጆችን ቁጥጥርና ክትትል ማሳደግ ኩረጃን ለማስቀረት ከሚከናወኑት አበይት ተግባራት መካከል ተነስተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ በሀገር አቀፍ መድረኮች ትግል እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡ የሀገር አቀፍ ፈተና ፈታኞች፣ የፈተና ኃላፊዎች እና ሱፐርቫይዘሮች በጥንቃቄ እንዲመለመሉ፣ የፈተና ደንብ ጥሰት ሲፈጸም ተገቢው እርምት እንዲወሰድ እና የፈተና ሥርዓት ጉድለት የሚፈጥሩትን በሕግ ጭምር ተጠያቂ ለማድረግ ነው በጋራ እየሠሩ የሚገኙት፡፡

ኩረጃ በሁሉም የትምህርት ደረጃ እየተፈታተነ ያለ ሀገር ዓቀፍ ችግር በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous article‹አረንጓዴው ዘብ› እየተፈተነ ነው፡፡
Next articleሕዝቡ ሰርጉን ለሚያደምቅበት፤ መንፈሱን ለሚያድስበት እና የሥርዓት ማረቂያ የሆነውን የአዝማሪነት ሙያ ማዘመን እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።