
ደሴ: ነሃሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ በተፈጠረ አለመረጋጋት በመንግሥት ተቋማት ላይ ዘረፋ እና ውድመት መፈጸሙን የወረዳዉ አሥተዳደር አስታውቋል፡፡
ለጋምቦ ወረዳ አሥተዳዳሪና የአቃስታ ከተማ እና የለጋምቦ ወረዳ ኮማንድ ፖስት አባል ቴዎድሮስ አበበ በተፈጠረው አለመረጋጋት በወረዳዉ 7 የመንግስት ተቋማት ላይ ዘረፋ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ በተለይ የፍትሕ ተቋማት ኾን ተብሎ የዘረፋዉ ኢላማ እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በወረዳዉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ ከተዘረፉና ከወደሙ መሥሪያ ቤቶች ውጭ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች አገልግሎት መጀመራዉንም ገልጸዋል፡፡
የወረዳዉ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ከተዘረፉ ተቋማት አንዱ ሲኾን የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊና የኮማንድ ፖስቱ አባል ኢንስፔክተር መሀመድ አደም ኮምፒዉተሮችን ጨምሮ የተለያዩ የጽሕፈት ቤቱ የመሥሪያ ቁሳቁስ እንደተዘረፉ ተናግረዋል፡፡
ከፖሊስ ጽሕፈት በተጨማሪ ፍርድ ቤት ፤ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት እና ሰላምና ደኀንነት ጽሕፈት ቤት ተመሳሳይ ዘረፋ እና ዉድመት ደርሶባቸዋል፡፡
የአማራ ሕዝብን ጥያቄ በሰላማዊ አማራጭ ብቻ እንጂ በመሰል ድርጊት ማስመለስ አይቻልም ብለዋል ፡፡
የአቃስታ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የአቃስታ ከተማ አሥተዳደርና የለጋምቦ ወረዳ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ብርሃን ሽመልስ በበኩላቸው በከተማዋ ሕዝብ አገልግሎቶች መጀመራቸዉን አረጋግጠዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!