
ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በየጊዜው የሚነሳው የጸጥታ ችግር የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በእጀጉ እየጎዳው መኾኑንም የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል የጸጥታ ችግር ከነበረባቸው ከተሞች መካከል ላሊበላ አንደኛዋ ናት፡፡ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች የኑሮ መሠረታቸው ቱሪዝም ነው፡፡ ከከፍተኛ ባለሀብቶች ጫማ እስከሚያስውቡ የከተማዋ ነዋሪዎች ድረስ ቱሪዝም የሕይወታቸው መሠረት ነው፡፡ የሰላም ችግር በተከሰተ ቁጥር የላሊበላ ነዋሪዎች የኑሮ መሠረት የኾነው ቱሪዝም ይቀዛቀዛል፡፡ ቱሪዝም ሲቀዛቀዝ ደግሞ ነዋሪዎቹ የኑሮ ሁኔታቸው ይናጋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ እና የወረራው ጦርነት ያስከተለው ችግር የላሊበላን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በእጅጉ ጎድቶት ቆይቷል፡፡ በመካከል በተፈጠረው ሰላም የቱሪዝም እንቅስቃሴው መነቃቃት አሳይቶ ነበር፡፡
በቅርቡ በከተማዋ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር አሁን ላይ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ቢሸጋገርም የላሊበላን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዳይጎዳው ስጋት ፈጥሯል፡፡
ላሊበላ ሰሞኑን ተፈጥሮባት ከነበረው የጸጥታ ችግር ወጥታ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ ላይ መኾኗን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ አንጻራዊ መረጋጋት መኖሩን እና መደበኛ እንቅስቃሴዎች እየተከወኑ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ የሦስት እግር ተሸከርካሪዎች (ባጃጆች) አገልግሎት እየሠጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከተማዋ የምትተዳደረው በቱሪዝም ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ቱሪዝሙ መጎዳቱንም ገልጸዋል፡፡ ሰላም ከሌለ የእንግዶች ማረፊያ የኾነችው ከተማዋ እንግዶችን እንደምትናፍቅም ነው የተናገሩት፡፡
አሁን ላይ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ እየመጡ አለመኾናቸውም ገልጸዋል፡፡ ሰላሙ አሁን በጀመረበት የበለጠ እየጸና ከሄደ የቱሪዝም እንቅስቃሴውም እንደሚሻሻል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡ ላሊበላ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጀምሮ ያንን ውብ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል በሚገባ እንግዶቿን እየተቀበለች ማሳየት አልቻለችም ነው ያሉት፡፡ የተሻለ ነገር ይመጣል ሲባል በየጊዜው የሚነሳው የጸጥታ ችግር ከተማዋን በኢኮኖሚ እየጎዳት መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
የቱሪዝም እንቅስቃሴው በመቀዛቀዙ መንግሥትም ከባለሀብቶች ሊሰበሰበው የሚችለውን ገቢ መሰብሰብ እንደማይችል ነው የተናገሩት፡፡ ላሊበላ ከቱሪዝም ውጭ ተለዋጭ የኾነ የገቢ ምንጭ የላትም ያሉት ነዋሪዎቹ ሰላም የማይረጋገጥ ከኾነ አደጋ ውስጥ እንደምትወድቅም ገልጸዋል፡፡
በላሊበላ ለመኖር እና የተሰበረውን ኢኮኖሚ ለመጠገን ሁሉም ለሰላም መሥራት እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ እርስ በእርሳችን ተግባብተን፣ ተፈቃቅረን እና ችግሮቻችን በውይይት ፈትተን ሰላምን መፍጠር አለብን ነው ያሉት፡፡
ሰላም ካልተፈጠረ ከተማዋ መነቃቃት እንደማትችል እና ሕዝቡም በኢኮኖሚ በእጅጉ እንደሚጎዳ ነው የተናገሩት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!