
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 20/2012ዓ.ም (አብመድ) አዝማሪነት ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን መጻሕፍት ጭምር እንደተመላከተው ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የማኅበረሰብ ማረቂያ፣ የነገሥታት ውሎን በግጥሞች ለትውልድ ማስተላለፍያ ሙያ ነው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴአትር እና ፊልም ጥበባት መምህር ባቀረቡት ጥናት ‹‹አዝማሪዎች አሁን ያለ የማኅበረሰብ ምሥጢርን ከመግለፅ ባሻገር ነገን መተንበይ የሚችሉ የፈጠራ ባለቤቶች ናቸው›› ብለዋል።
በኢትዮጵያ አዝማሪዎች በንግሥት ሳባ ዘመን እንደገባ መረጃዎች እንዳለ ያመለከቱት መምህር ምስጋናው ‹‹በዘመናቱ ጎንጦ የማያቆስል፤ ማኅበራዊ ሂስ ማስኪጃ ሁኖ ኖሯል›› ብለዋል።
ለአዝማሪነት የተመሳሳይ ግጥሞች መኖር፣ የስብሰባ ማድመቂያ ብቻ መሆንና ቴክኖሎጂው ማነቆ እንደሆነ ተናግረዋል። ‹የበረሁ የአዝማሪዎች ማኅበር› ሰብሳቢ ዓለም አጫዋች ወረታው ዓለሙ ‹‹ቀድሞ አዝማሪ ‹ምን አለ? ምን ሊናገር ነው?› ተብሎ ይጠበቅ ነበር፤ አሁን ግን ‹አታደንቁረኝ› የሚሉት ይበዛሉ›› ብለዋል። በዚህ ምክንያት የአዝማሪዎች ቁጥር መቀነሱን ተናግረዋል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የቴአትርና ፊልም ጥበባት መምህር አስናቀው ዓለሙ ‹‹ሕዝቡ ሰርጉን ለሚያደምቅበት፤ መንፈሱን ለሚያድስበት እና የሥርዓት ማረቂያ ለሆነለት የአዝማሪነት ሙያ ማዘመን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል›› ብለዋል።
መንግሥት የሙያ ማኅበራትን ማቋቋምና ካላቸው ፋይዳ አንፃር ማጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል።
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው ሠላም የባህል መድረክ ምክክር ለአዝማሪዎች ክብርና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ መንግሥት በጥበብ ፈንድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባውም ተመላክቷል።
አዝማሪነት ጥበብን ማፍለቅ፣ ምስጢርን መግለፅ እና የደስታ ምንጭ መሆኑን በማስገንዘብ የተዛቡ አመለካከቶች ተቀርፈው የኢኮኖሚ ምንጭ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
‹ሠላም ኢትዮጵያ› የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከደብረ ታቦርና ጎንደር ዮኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ዘርፉን ለማሳደግ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ዛሬ ምክክር ተደርጓል።
ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ ―ከደብረ ታቦር