“በክልሉ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት የሁሉም ፕሮጀክቶች መደበኛ ሥራ ተስተጓጉሏል” የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ

52

ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በፌዴራልና በክልሉ መንግሥት የሚሠሩ የድልድይ ፣ የመንገድና የመስኖ ፕሮጀክቶች በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት መደበኛ ሥራቸውን መሥራት እንዳልተቻለ ነው ቢሮው ለአሚኮ ያስታወቀው።

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ በትግሉ ተስፋሁን እንደተናገሩት ክልሉ ከዚህ ቀደም በሰሜኑ ጦርነት የተጓተቱ ፕሮጀክቶች እንደነበሩ አንስተዋል። አሁን ደግሞ በክልሉ በተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኙ ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜና ገንዘብ ለማጠናቀቅ እንዳይቻል እንቅፋት ኾኗል ነው ያሉት።

ከ90 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በክልሉ 60 የሚደርሱ የፌዴራል ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደኾነ የተናገሩት ኀላፊው በሰላምና አለመረጋጋት ምክንያት ሁሉም መደበኛ ሥራቸው እንደቆመ ነው የተናገሩት።

ክልሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ ሲመለስ በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባትም በቢሮ ደረጃ የሚሠሩ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን አንስተዋል።

የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ፕሮጀክቶች በሰላም እጦት እየተስተጓጎሉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት ኀላፊው።

ግጭትና አለመረጋጋቱ በዋግኽምራ ፣ ደቡብ ወሎ ፣ ምሥራቅ ጎጃም ፣ ሰሜን ጎንደር ፣ ምእራብ ጎጃም እና ሌሎችም የክልሉ ዞኖች የክልልና የፌዴራል ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ልክ እንዳይሠሩ እያደረገ ነው።

ሰላም ለመንገድ ለተሳለጠ የመሰረተ ልማት ሥራ ወሳኝ ነው የሚሉት አቶ በትግሉ በከፍተኛ የሕዝብ ጥያቄ ግንባታቸው የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ተሠርተው ለአገልግሎት እንዲበቁ ሁሉም ለሰላምና መረጋጋት የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በተለይም ከአደሩ ፕሮጀክቶች ባሻገር በ2016 በጀት ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር የሚሠራበት ወቅት ነው ያሉት ኀላፊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ፣ የዲዛይን ጥናትና ዝግጅት ፣ መረጃ የሚሰበሰብበትን ኹኔታ እያስተጓጎለ ነው ብለዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ወደ 14 አዳዲስ ፕሮጀክቶችና ያደሩ 30 የሚደርሱ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እንደሚሠራም ነው የተናገሩት።

ቢሮው ክልሉ ወደ ሰላሙ ሲመለስ የተስተጓጎለውን ጊዜ በሚያካክስ መልኩ ለመሥራት ጥረት ያደርጋል ነው ያሉት።

አሁን ባለው አንጻራዊ ሰላም በቢሮ ውስጥ የሚሠሩ የማመቻቸትና የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ተብሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረ ብርሃን ከተማ በወቅታዊ የጸጥታ ኹኔታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ከባጃጅ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ጋር ተካሄደ።
Next articleላሊበላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ መኾኗን ነዋሪዎቹ ተናገሩ፡፡