በደብረ ብርሃን ከተማ በወቅታዊ የጸጥታ ኹኔታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ከባጃጅ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ጋር ተካሄደ።

31

ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በውይይቱ የባለሦስት እግር አሽከርካሪዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተቀመጠውን ክልከላ አክብረው እንዲሠሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

በደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ችግር የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፤ ምጣኔ ሀብታዊና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎችም ሙሉ በሙሉ ችግር ውስጥ እንደነበር ተገልጿል።

በቅርብ ዓመታት ጥሩ ሁለንተናዊ መነቃቃት የታየባት ደብረብርሃን ከተማ የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የቱሪዝም ዘርፎች ከሥራ ውጪ እየኾኑ መምጣታቸውም ተጠቅሷል።

የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት አባሉ በድሉ ውብሸት እንዳሉት የትራንስፖርት እንቅስቃሴም ተገድቧል።

በዚህም ወደ ከተማዋ ለመሠረታዊ ፍጆታ የሚኾን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማስገባት አዳጋች ኾኗል ነው ያሉት። ይህም የኑሮ ውድነቱ ይበልጥ እየተባባሰ እንዲሄድ ያደርጋል፣ በዚህ ችግር የሚፈተኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለተጨማሪ ጉዳት ይዳርጋል፣ የሰላም መደፍረስ ችግር እንዲፈጠርም ተጨማሪ ምክንያት ሊኾን እንደሚችል አመላክተዋል።

አቶ በድሉ እንዳሉት የተወሰኑ የባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ለጸጥታ ችግር መባባስ መንስኤ ኾነው ተገኝተዋል። በነዚሁ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ግድያ፣ ስርቆት እና አጠቃላይ የወንጀል ድርጊቶች መበራከት ታይቷል። ባመዛኙ ስምሪት የሌላቸው እና ሰሌዳ ያልተለጠፈላቸው ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን ለዚህ ተግባር በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በዚህ መነሻነትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ክልከላ መሰረት እንዲጣል ኾኗል። ይሁንና በትራንስፖርት ዘርፉ አገልግሎት በመስጠት በሚተዳደሩና ቤተሰባዊ ኀላፊነት ባለባቸው ግለሰቦች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዳግም ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።

ይህንን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስቀመጣቸውን ክልከላዎች አክብረው እንዲሠሩም አቶ በድሉ አሳስበዋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ ባለሀብቶችም የሰላም እጦት የፈጠረው ገደብ ለችግር እንዳጋለጣቸው ጠቅሰዋል።

ወደ ሥራ በመመለሳቸው መደሰታቸውን በመናገርም ሕግና ሥርዓትን አክብረው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሠላም እጦት የበደለው ሕብስት”
Next article“በክልሉ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት የሁሉም ፕሮጀክቶች መደበኛ ሥራ ተስተጓጉሏል” የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ