
ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አበው የሰሩት ታሪክ፣ ተፈጥሮ የለገሰው ድንቅ ውበት ለአማራ ክልል ድንቅ በረከቶች እና ስጦታዎች ናቸው፡፡ ከመተማና ቋራ፣ ከዳንሻና ሑመራ ሞቃታማ ስፍራዎች እስከ ራስ ደጀን ተራራ ቀዝቃዛማ ሥፍራዎች የሚገኙበት ምድር ነው፡፡
ጥንታዊ አብያተመንግሥታት፣ አብያተክርስቲያናት፣ገዳማት፣ መስጂዶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች፣ተፈጥሮ ሞሽሮ የሠራቸው ውብ ሥፍራዎች፣ለዘመናት የኖሩ እና የተከበሩ ድንቅ ባሕሎች፣ ለዘመናት ትውልድን ከትውልድ ጋር አስተሳስረው የኖሩ ውብ እሴቶች ያሉበት ነው የአማራ ክልል፡፡
በአማራ ክልል ሰላም ሲኖር የቱሪዝም ሃብት በመሶብ እንደ ቀረበ ሕብስት ነው፡፡ ሰላም ሲኖር በፍቅርና በደስታ በጋራ ኾኖ ከሕብስቱ መብላት፣ ከወይኑም መጎንጨት ነው፡፡ ለምን ካሉ የበዙ ጎብኚዎች ባሕር አቋርጠው፣ የብስ ሠንጥቀው ወደ ድንቁ ምድር የሚመጡ አሉና፡፡
የአማራ ክልል በወረኃ ነሐሴ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት በስፋት የሚከበሩበት ክልል ነው፡፡ ሻደይ፣ አሻንድዬ፣ ሶለል፣ እንገጫ ነቀላ፣ የቡሔ በዓል ወይም በዓለ ደብረታቦር፣ የእምዬ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ በዓለ ልደት የሚከበርበት በርካታ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ የሚገቡበት ነው፡፡
በእነዚህ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት የክልሉ ሕዝብ ታሪኩን፣ ባሕሉን እና ሃይማኖቱን ለዓለም ያስተምርባቸዋል፡፡ ውበቱን፣ እንግዳ ተቀባይነቱን፣ ጀግንነቱን፣ ታሪካዊነቱን፣ የጥበብ ሃብቱን፣ አርቆ አሳቢነቱን፣ ታሪክ ጠባቂነቱን፣ ሰው አክባሪነቱን እና ትዕግሥቱን ያሳይባቸዋል፣ ለዓለም ሁሉ ያስተምርባቸዋል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የሚኾነው ሰላም ሲኖር፣ የሰላም መንገዶች ሲከፈቱ እና ጎብኚዎች ወደ ክልሉ ሲመጡ ነው፡፡
የአማራ ክልል ሰላም ሲኖር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ክልሉን ይጎበኙታል፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ ደግሞ ይገኝበታል፡፡ አሁን ወረኃ ነሐሴ ደርሷል፣ ብዙዎች ተወዳጅ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ በዓላትን ለማክበር ሲጓጉ ከርመዋል፡፡ ባሕር አቋርጠው፣ የብስ ሰንጥቀው በዓላቱ ወደሚከበሩበት እና ወደ ሚከወኑበት ሥፍራ ለመሄድ ጓጉተዋል፡፡ በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት ግን ለዓመት የጓጉለትን እና በተስፋ የጠበቁትን እንዳያከብሩ መሰናክል ይኾንባቸዋል፡፡
የአማራ ክልል በመሶብ የተቀመጠ ሕብስት አለው፤ ከሕብስቱ እንዳይመገብ ግን የሰላም እጦት እንቅፋት ኾኖበታል፡፡ በአማራ ክልል ሰላም ብቻ ካለ ቢሊዮን ብሮች ይገባሉ፡፡
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢአለ እንዳሉት በክረምት ወራት በክልሉ በርካታ ሁነቶች ይካሄዳሉ፡፡ የቡሔ በዓል ወይም ደብረ ታቦርን በደብረታቦር፣ ሻደይ በዋግኸምራ፣ አሸንድዬ በላስታ ላሊበላ፣ ሶለል በራያ ቆቦ፣ እንገጫ ነቀላና ከሴ አጨዳ በምሥራቅ ጎጃም በድምቀት ይከበራሉ፡፡ በዓላቱ የሕዝቡ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች መገለጫዎች መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት የልጃገረዶች ነጻነት የሚገለጽባቸው በዓል መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በዓላቱ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን እንደሚስቡም ነግረውኛል፡፡ የቱሪስት መሳብ አቅማቸው የተዋጣላቸው መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል በ2015 በጀት ዓመት 15 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች ክልሉን ጎብኝተውታል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከ5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች የጎበኙት በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ የተገኘበት በክልሉ ሰላም ስለነበር ነው፡፡ ሰላም ሲኖር ሚሊዮኖች ወደ ክልሉ ያቀናሉ፣ ቢሊዮን ብርም ለክልሉ ያስገኛሉ፡፡ በዓለፈው ዓመት በክልሉ ሰላም ስለነበር በወረኃ ነሐሴ የሚከበሩ በዓላት በድምቀት መከበራቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ያም ኾኖ የነበረው የወረራ ጦርነት ጥላውን እንደጣለበት ስለነበር የውጭ ጎብኚዎች በሚፈለገው ልክ አለመምጣታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
አስተማማኝ ሰላም ሲፈጠር በክልሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ክልሉ እንደሚመጡም ገልጸዋል፡፡ ሰላም ሲታጣ የውጭ ጎብኚዎች ብቻ ሳይኾን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችም ወደ ክልሉ እንደማይመጡ ነው የተናገሩት፡፡ የጎብኚዎች መቅረት ክልሉን ገቢ እንደሚያሳጣውም ተናግረዋል፡፡
ሰላም ሲጠፋ የአማራ ክልል ከሚገጥመው የገንዘብ ኪሳራ ባለፈ የገጽታ ግንባታውን እንደሚያበላሸውም ገልጸዋል፡፡
ማራኪ መስሕቦች፣ የትራንስፖርት አቅርቦት፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማት የቱሪዝም ግብዓቶች ናቸው ያሉት ኀላፊው ሰላም ግን የቱሪዝም ዋነኛው ግብዓት ነው ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል የማራኪ መስሕቦች ሀብት ባለቤት ነው፣ ዋና ዋና የሚባሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች የትራንስፖርት አገልግሎት አላቸው፣ ሰላም ከሌለ ግን ቱሪዝም የሚባል ነገር የለም ነው ያሉት፡፡ ቱሪዝም በባሕሪው የሰዎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደሚጠይቅ የተናገሩት ኀላፊው ቱሪዝም አንድ ጥይት እንደተተኮሰ የሚቆም ዘርፍ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ሰዎች ሳይንቀሳቀሱ ቱሪዝምን ማሰብ እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት የነበረው ሰላም ዘንድሮም ቢኖር ኖሮ በወረኃ ነሐሴ የሚከበሩ በዓላት ለክልሉ ገቢ በማስገኘትና ገጽታን በመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖራቸው እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡ አስተማማኝ ሰላም ባለመኖሩ ቢሮው በደመቀ ሁኔታ ለማክበር እንደሚቸገርም ገልጸዋል፡፡ በዓላቱን እንግዶች መጥተው ባያከብሩትም እንኳን በአካባቢው ባሕላዊነታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ እንግዶች ባለመምጣታቸው ግን ከእግዶች ሊገኝ የሚችለው ገቢ እንደማይገኝ ነው የተናገሩት፡፡ ለሰላም ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
በሰላም እጦት ምክንያት ገቢያቸው በቱሪዝም ላይ የተመሰረቱ አካባቢዎች ገቢ እንደሚያጡም ገልጸዋል፡፡
የሰላም መደፍረስ የማይጎዳው የኅብረተሰብ ክፍል የለም ያሉት ኀላፊው ሰላምን በማጽናት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ሰላም እንዲኖር መንግሥትና ሕዝብ በጋራ መሥራት ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡ ትርፎች ሁሉ ያሉት ከሰላም መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ችግሮችን በውይይት በመፍታት ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል አጓጊ የቱሪዝም መዳረሻዎች እና የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉት የተናገሩት ኀላፊው ሰላም ሲታጣ ማኅበራዊ ቀውስ እንደሚፈጠርም ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ስለ ሰላም መስበክ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ ሰላም ከሌለ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ነገሮችን እናጣለን ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል ማግኘት የሚገባውን እንዲያገኝ ችግሮችን በምክክር እና በራስ አቅም መፍታት ይባልም ብለዋል፡፡
ሰላምን ጠብቁት፣ አስጠብቁት በመሶብ ያለውን ሕብስትም በፍቅርና በአንድነት ተመገቡት፡፡ ሰላም ለሁሉም ታስፈልጋለች፣ ሰላም ሁሉም ይጠብቃት ዘንድ ትፈልጋለች፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!