የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የአብሮነት እሴቶችን በማስጠበቅ ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ሀገራዊ ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

83

ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የአብሮነት እሴቶችን በማስጠበቅ ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ሀገራዊ ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊና የጎንደር ቀጣና ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ደሳለኝ ጣሰው ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በኅብረተሰቡ የጋራ ጥረት ወደ ሰላምና መረጋጋት እየተመለሰ ነው።

በወቅቱ የነበረው የጸጥታ ችግር በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥራ ለመፍታት አዳጋች በመኾኑ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ታውጆ በአጭር ጊዜ ሁሉንም አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለስ ተችሏል።

አጠቃላይ የነበረውን የጸጥታ ችግር በማስመልከት በጎንደር ከተማ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውይይት ማድረግ ጀምረዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊና የጎንደር ቀጣና ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ደሳለኝ ጣሰው፤ የጋራ ውይይቱ ዓላማ በጋራ ችግሮች ላይ መፍትሄ ለመሻት መኾኑን ገልጸዋል።

በመኾኑም የሕዝብ ጥያቄዎች ሊፈቱ የሚችሉት በውይይትና በመደማመጥ በመኾኑ ዘላቂ ሰላም የመፍጠር ጉዳይ የሁሉም አጀንዳ ኾኖ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በትውልድ ግንባታ ላይ የላቀ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው የአብሮነት እሴቶችን በማስጠበቅ ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ሀገራዊ ልማት እንዲሠሩ ኀላፊው ጠይቀዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩ አቡሀይ በበኩላቸው በነዋሪዎች የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከተማ አሥተዳደሩ በቁርጠኝነት የሚሠራ መኾኑን አረጋግጠዋል።

ባለፈው ሳምንት በከተማዋ የተፈጸመው ድርጊት ሕዝቡን የማይወክል መኾኑን ጠቅሰው በቀጣይ መሰል ክስተቶች እንዳይኖሩ በጋራ መታገል አለብን ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበወገልሳ የተቀናጀ የአሳ ግብርና ኘሮጀክት ላይ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት መድረሱን ተቋሙ ገለጸ፡፡
Next article“የሠላም እጦት የበደለው ሕብስት”