
ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን ከተማዋ ደብረ ታቦር ከቀናት በፊት ገጥሟት ከነበረው ግጭት እና አለመረጋጋት ሙሉ በሙሉ ወጥታ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደምትገኝ ነዋሪዎቿ ተናግረዋል።
በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ሱቆች፣ ባንኮች፣ ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች ወትሯዊ መስተንግዷቸውን እየሰጡ ስለመኾኑም ተገልጿል።
“የደብረ ታቦር ሕዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ሁነኛ ደጀን ነው፤ ይህም በሠራዊት አባላት ልብ ላይ በደማቅ ተጽፏል” ያሉት የከተማዋ ነዋሪ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ከተማዋ ገብተው ሕዝብን የማረጋጋት ሥራ እየሠሩ ነው ብለዋል። ሕዝቡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን በሰላም ተቀብሎ በፍጹም መግባባት ለከተማዋ ሰላም በጋራ እየሠራ ስለመኾኑም ተገልጿል።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ከነዋሪዎች ጋር ተወያይተው ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ መቻሉንም ነው የነገሩን።
እንደነዋሪዎች ገለጻ ግጭት የወለደውን የሰላም እጦት ተከትሎ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር ነጋዴዎችም ኾኑ ሸማቾች በመመካከር እና በኀላፊነት እየሠሩ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!