
ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሞኑ አለመረጋጋት ምክንያት በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ጭማሪ መስተዋሉን የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የዋጋ ጭማሪ እንደሚኖር ቢገነዘቡም የዋጋ ጭማሪው ያልጠበቁት እንደኾነባቸው ነው የተናገሩት፡፡
አለመረጋጋቱን ምክንያት በማድረግም ሕገወጥ ነጋዴዎች በባሕርዳር ከተማ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች ከነበረው ዋጋ እንዲጨምር በማድረግ የዋጋ ንረት እንዲባባስ አድርገዋል ብለዋል ነዋሪዎች፡፡
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የሰላም እጦት በምርት አቅርቦት ላይ የሚፈጥረው እጥረትን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ እንደሚኖር ቢገነዘቡም የዋጋ ጭማሪው ያልጠበቁት እንደኾነባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
ኅብረተሰቡ በችግር ጊዜ እርስ በእርስ መተዛዘን እንደሚገባቸው ተናግረው ሰላም የሁሉም መሰረት በመኾኑ ሰላሙን መጠበቅ አስፈላጊ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡
ነጋዴዎች በበኩላቸው በሰላም እጦት ምክንያት መንገድ በመዘጋጋቱ የምርት እጥረት ማጋጠሙን አስረድተዋል፡፡
የዋጋ ጭማሪውም ከምርት አቅርቦት ጋር እንደሚያያዝ ገልጸው ምርት ወደየ አካባቢው በነጻነት እንዲዘዋወር ሁሉም ሰው ለሰላም ማስከበር ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ለዚህም መንግሥት እና ሕዝብ በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡
የአማራ ክልል ንግድ ገቢያ ልማት ቢሮ በበኩሉ የሰላም እጦቱ በምርት እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንዳለ ኾኖ ነጋዴዎች ያለውን ምርት በአቋራጭ ለመክበር በተጋነነ ዋጋ ለመሸጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተገቢ እንዳልኾነ ገልጾ ነጋዴዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስቧል፡፡
ቢሮው ሕግ ለማስከበርም አስፈላጊውን ቁጥጥር እንደሚያደርግም መግለጹ ይታወሳል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!