‹አረንጓዴው ዘብ› እየተፈተነ ነው፡፡

303

‹አረንጓዴው ዘብ› እየተፈተነ ነው፡፡

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 20/2012ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ሥፍራዎች መካከል ይጠቀሳል፤ የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ። ፓርኩ በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በበረሃማው ክፍል ይገኛል። የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በአማራ ክልል ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 38/1998 ዓ.ም ነው የተቋቋመው።

የቋራ ወረዳን አንድ ሦስተኛውን ማለትም 266 ሺህ 570 ሄክታር ይሸፍናል። በምዕራብ በኩል ከሱዳኑ የዲንደር ብሔራዊ ፓርክ ጋር የ78 ኪሎ ሜትር ድንበር ይጋራል፡፡ በደቡብ በኩል ደግሞ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኘው የቢጃሚስ ፓርክ እንዲሁም በሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ ደግሞ በቋራ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙት ከሰባት ያላነሱ ቀበሌዎች ጋር ይዋሰናል።

በፓርኩ 32 አጥቢ እንስሳት፣ 17 የዓሣ ዝርያዎች፣ ስምንት ተሳቢና ተራማጅ እንስሳት፣ ከ240 ያላነሱ የአዕዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ 11 የሳር ዓይነቶች፣ 14 የቁጥቋጦና 57 ትልልቅ ዛፍ ዓይነቶችም ይገኙበታል። በተጨማሪም ፓርኩ ዛፎች ላይ የሚገኝ የጫካ ማር፣ የእጣንና ሙጫ ዛፎች እንዲሁም የተለያዩ ለምግብነት የሚውሉ የዱር ፍራፍሬዎችን የታደለ ነው፡፡ ለአብነት ወይን፣ ሲንሳ፣ አሻማ፣ እንኮይ፣ ኮመርና ዲዛ ፍራፍሬዎች ይገኛሉ።

በአፍሪካ በመጥፋት ላይ ያለው ባለ ጥቁር ጋማ አንበሳ መኖሩም ፓርኩን ለየት ያደርገዋል። ከአዕዋፋትም ትልቁ ሰጎን እንደሚገኝ ይነገራል። በሌላ በኩልም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥ ዘ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ የስደት መልስ ለሰባት ቀናት ያረፉበት ውስጡ የተቦረቦረ በአካባቢው አጠራር ‹ዲዛ› የሚባል ትልቅ ዛፍም መገኛ ፓርክ ነው።
በዘርፉ ጥናት ባደረጉ ምሁራን የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በፍጥነት እየተስፋፋ ያለውን የሰሃራ በረሃ ተፅዕኖ ይገታል ተብሎ ተስፋ ስለተጣለበት ‹‹አረንጓዴው ዘብ›› ብለው ይጠሩታል። ተባባሪ ፕሮፌሰር ገናናው ‹‹የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ሕይወት፣ ሀብትና ውበት ነው›› ሲሉም ይገልፁታል። ለብዙ የዱር እንስሳት መጠለያና የሕይወት ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር ለአካባቢው ንፁህ አየርን ይመግባል። ፓርኩን ከ20 ሚሊዮን ቶን ያላነሰ ካርበንን መምጠጥ የሚችል ነው፤ ይህም በገንዘብ ቢተመን እስከ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚገመት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።

ምንም እንኳ ፓርኩ ይህን መሠል ዕምቅ ሀብቶችን የያዘ ቢሆንም የተስፋ ምድር ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ስጋት መፈጠሩም አልቀረም። ተመራማሪው እንዳሉት ፓርኩ አሁን ላይ በብዙ ችግሮች እየተፈተነ ነው፡፡ ፓርኩ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ተጋርጠውበታል፡፡ የሰደድ እሳት መስፋፋት፣ የሕገ ወጥ አደን መበርከት፣ የመሠረተ ልማት አለመኖር፣ ልቅ ግጦሽ፣ የደን ጭፍጨፋ፣ የመንግሥት ትኩረት መጓደል፣ የሞፈር ዘመት አራሾችና የቀንድ ከብቶቻቸው ዘልቆ መግባት ውስጣዊ ችግሮች ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡

ወንዞችን በመመረዝ የዓሣ ዝርያዎችን ማመናመንና ውኃውን የሚጠጡ የዱር እንስሳትን ለሞት መዳረጉ፣ ከፓርኩ ድንበር አከላለል ጋር የተያያዙ የአካባቢው ማኅበረሰብ ቅሬታዎች፣ አካባቢው ለሰፈራ ተጋላጭ መሆኑ በዋናነትም በ1995 ዓ.ም አካባቢ ፓርኩ ድንበር ላይ የተደረገው የሰፈራ መርሀ ግብር ሌሎች ፈተናዎች ናቸው።

ምሁሩ ውጫዊ ችግሮች ብለው ከጠቀሷቸው መካከል ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው የሚገቡ ድንበር ዘለል እንስሳት አርቢዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጀሪያ የሚነሱት የፉላኒ ጎሳ ክፍል የሆኑት ፈላታዎችና ከሱዳን የሚመጡት ሩጣና እና መሳሊጥ እየተባሉ የሚጠሩት ጎሳዎች የፓርኩ ስጋት መሆናቸውን አስረድተዋል። እነዚህ እንስሳት አርቢ ጎሳዎች በአራት የጎሳ አስተዳደሮች ይመራሉ፡፡ ከ410 ያላነሰ ቤተሰብ ወይም ከሁለት ሺህ በላይ ግለሰቦችንም ያካትታሉ። ጎሳዎቹ በዋናነትም ከብት አርቢዎች ስለሆኑ ከ800 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚገመቱ የቀንድ ከብቶችን በፓርኩ ያሠማራሉ፡፡ ሕገ ወጥ የእንስሳትና የጦር መሣሪያ ንግድም ያካሂዳሉ፡፡ የዱር እንስሳትን በማደንና ለእንቅስቃሴያቸው ያመቻቸው ዘንድ ጫካውን በእሳት በማቃጠል የፓርኩን ኅልውና አደጋ ላይ ጥለውታል።

ተመራማሪው መንግሥት የፓርኩን መሠረተ ልማት በማሟላትና ያካባቢውን ማኅበረሰብ ከፓርኩ ጋር የሚያስተሳስር ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም እንዲኖር ማስቻል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ለምሳሌ የዓሣ፣ ማር፣ የዱር ፍራፍሬዎችን፣ የእጣንና ሙጫ ምርት እንዲሁም የጣውላ ውጤቶችን ፓርኩን በማይጎዳ መልኩ መጠቀም እንደሚቻል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይ ወጣቶች እንዲጠቀሙባቸውና በፓርኩ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ እንደሚቻልም አውስተዋል። ፓርኩ የሀገሪቱን የቱሪዝም ልማት በማሳደግ ረገድና የገቢ ምንጭ በመሆን የራሱ አስተዋፅኦ አለው ተብሏል።

በፓርኩ የማኅበረሰብና ቱሪዝም ባለሙያ አቶ ስመኘው ውበት ከማኅበረሰቡ ጋር ተከታታይ ውይይቶችን እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ‹‹የአካባቢው ኅብረተሰብ የባለቤትነት ስሜት እያደገ ነው›› ተብሏል፡፡ በቋራ ወረዳ የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ወንዴ ደግሞ ፓርኩ የሰው ኃይል እና የግብዓት እጥረት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል የፓርኮችና የዱር እንስሳት መጠለያ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት የሰሜን ቀጠና አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ተክሉ የፓርኩን የሰው ኃይል ለመጨመር እና ጥቅማጥቅም ችግር ለመፍታት አዲስ መዋቅር ለመዘርጋት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም የእንስሳት አርቢ ጎሳዎችን ተፅዕኖ ለመቀነስ ከሱዳን መንግሥት፣ ከኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ በዚህም ወደ ፓርኩ ሰርገው መግባት አቁመዋል የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ ቅሬታዎችን ለመፍታትም ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል። በአጠቃላይ ከፓርኩ ጋር የተያያዙ ተጨማሪ ችግሮችን ለመፍታት በቅርቡ ጠለቅ ያለ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡- ባበይ ፀሐይ
ፎቶ፡- ከድረ ገጽ

Previous article‹‹ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ምንነት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡›› ወጣቶች
Next articleኩረጃን ለማስቀረት የአማራ ክልል መምህራን ማኅበር፣ የተማሪ ወላጆች ማኅበርና የክልሉ ትምህርት ቢሮ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን አስታወቁ፡፡