አሁንም የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ እና ሽብር የሚነዙ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ተባለ፡፡

28

ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች እና የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት በወቅታዊ የፀጥታ ኹኔታ ከኮማንድ ፖስቱ መሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች መሠረታዊ በኾኑ የፀጥታ ጉዳዮች እና የመፍትሔ አማራጮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በከተማ አሥተዳደሩ ወቅታዊ የጸጥታ ችግሮች ዙሪያ ለውይይት መነሻ የሚኾን ሃሳብ አንስተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ እና ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉት ይታወቃል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ችግሮቹ የሚፈቱት በሰከነ እና በሠለጠነ መንገድ መኾን ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

በቅርቡ የተስተዋለው የፀጥታ ችግር የክልሉን ሕዝብ መሠረታዊ ጥቅሞች አጋልጦ የሚሰጥ እና ኀይልን የሚበታትን ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ክንቲባው ካለፈው ተምሮ በውይይት እና በምክክር ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም ይገባል ብለዋል፡፡

አሁንም የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ እና ሽብር የሚነዙ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ያሉት ዶክተር ድረስ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እና የሕዝቡን የሥነ-ልቦና ልዕልና የማይመጥኑ ስግብግብ ድርጊቶችን በጋራ መታገል እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

ከባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የመነሻ ሀሳብ በኋላ ጥያቄ እና አስተያየት የሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች በክልሉ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የሰከነ እና ዘላቂ መፍትሔ ላይ ያነጣጠረ ውይይት እና ምክክር ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ተሳታፊዎቹ ከውይይት በኋላም ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች ሳይሸራረፉ ሊተገበሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡

መከላከያ ሕዝባዊ መሠረት ያለው የሕዝብ ተቋም ነው ያሉት የኮማንድ ፖስቱ አባል ኮሎኔል ሽፈራው ቢሊሶ ሠራዊቱን ከሕዝብ ለመነጠል የሚሰነዘሩ የሐሰት መረጃዎች መሰረት የላቸውም ብለዋል፡፡ ግጭቱ ከመፈጠሩ በፊት በውይይት እና በትዕግስት ለመፍታት እስከ ሽምግልና የደረሰ የሰላም ጥረቶች ተደርገው እንደነበርም ኮሎኔል ሽፈራው አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያን መስሎ የተሠራ እና የተዋቀረ ሠራዊት አንድን ብሔር ነጥሎ የሚያጠቃበት ሥነ-ልቦና የለውም ያሉት ኮሎኔል ሽፈራው ይኽን መሰሉ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እና ሽብር ዛሬ ብቻ ሳይኾን ትናንትም እንደነበር ይታወቃል ብለዋል፡፡ የአካባቢውን ሰላም እና የሕዝቡን ደኅንነት ለማስጠበቅ ቀን ከሌሊት የሚሠራውን ሠራዊት ቀርቦ ማየት እና አሠራሩን መረዳት ተገቢ እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ሠራዊቱ በየአካባቢው የመሯሯጥ እና በየበራፉ የመቆም አጀንዳ የለውም፤ የአካባቢውን ሰላም በአስተማማኝ ኹኔታ ለማረጋገጥ አሁንም እንደትናንቱ ከሕዝብ ጋር በጋራ ይሠራል ያሉት ኮሎኔሉ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ተቀራርቦ መነጋገር እና መወያየት ውድ ዋጋ ከመክፈል ያድናል ነው ያሉት፡፡ ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም ሕዝቡ ተባባሪ እና አጋር እንዲኾንም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተለያዮ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች በአካል ጉዳተኞች ፣ በህጻናት እና በሴቶች ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ መኾኑ ተገለጸ፡፡
Next articleከተማዋ ወደ መደበኛ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሷን የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።