
ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ሴቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ በሀገራችን ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች አሉ፡፡ በሀገራችን ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን የመሠረተ ልማት ግንባታ አለመኖር እና አገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግር እንደዳረጋቸው ይነገራል።
በመንገድ ላይ የቁም እና የወለል ምልክቶች እጦት፤ ወደ ሕንጻዎች አካል ጉዳተኞችን የሚደግፉ መወጣጫዎች እጦት፤ ተመጣጣኝ መጸዳጃ አገልግሎቶች አለመኖር በመጓጓዣ አገልግሎቶች ዘርፍ አካል ጉዳተኞች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች መኾኑናቸውን በተለያየ አጋጣሚ ይገልጻሉ፡፡
ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በአማራ ክልል አሁን የተፈጠረው የሰላም እጦት በክልሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ለተደራራቢ ችግር እንዳጋለጣቸው አሚኮ ያነጋገራቸው አካል ጉዳተኞች ተናግረዋል፡፡
መምህርት ማህሌት እጅጉ አይነ ስውር ናቸው፡፡ የልጅ እናት የኾኑት መምህርት ማህሌት የሰላም እጦት በአካል ጉዳተኞች በሴቶች እና በህጻናት ላይ የሚያሳድረው ጫና ከሌላው የኀብረተሰብ ክፍል በተለየ ኹኔታ ከፍተኛ መኾኑን ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ሰው የኾነ ሁሉ የሚፈልገው ነው የሚሉት መምህርት ማህሌት ለአካል ጉዳተኞች ፣ ለሴቶች እና ለህጻናት ደግሞ የሚኖረው ትርጉም የተለየ ነው ብለዋል፡፡ በታዳጊ ሀገር ለሚኖሩ አካል ጉዳተኞች ህጻናት እና እናቶች ካለው የኑሮ ጫና በተጨማሪ የሰላም እጦት ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥርባቸው ነው የተናገሩት፡፡ በተለይ በአነስተኛ ሥራዎች ለተሰማሩ አካል ጉዳተኞች ጫናው ከፍተኛ ነው የሚሉት መምህርት ማህሌት በሰላም እጦት ምክንያት በተፈጠረው የእንቅስቃሴ መገደብ ምክንያት በማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በእጅጉ ይፈተናሉ ብለዋል፡፡
ስለኾነም ውድ የኾነውን የሰላምን ዋጋ በመረዳት ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል በአሉባልታ ወሬዎች ባለመታለል ሰላም እንዲመጣ የመፍትሔ አካል መኾን ይገባናል ነው ያሉት፡፡ በተለይ ሚዲያዎች ሙያዊ ሥነ ምግባርን ያከበረ ሥራ በመሥራት ሰላም እንዲመጣ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ወጣት ዋለልኝ ክንዴ የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ ዋለልኝ በተቀጠረበት መሥሪያ ቤት በሥራ ቦታው እያለ ግጭት በመፈጠሩ ምክንያት በመሥሪያ ቤቱ እንዲያድር እና እንዲውል ተገድዶ ነበር፡፡ ዋለልኝ ካለበት የአካል ጉዳት ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት ለመንቀሳቀስ ፈትኖት እንደነበር አስታውሷል፡፡ ቢኾንም ግን ከቢሮ ወደ ቤቱ ከሦስት ሰዓት በላይ የፈጀ አድካሚ የእግር ጉዞ በኃላ ቤቱ መድረስ ችሏል፡፡
ወጣት ዋለልኝ እንደሚለው የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ አካል ጉዳተኞችን ከሌሎች የኀብረተሰብ ክፍሎች አንጻር በተለየ መልኩ ይፈትናል፡፡ ወጣት ዋለልኝ በሰላም እጦት ምክንያት ከጠፋው የሰው ሕይወት እና ንብረት ባሻገር በተለይም ከእጅ ወደ አፍ የሚኖሩ የኀብረተሰብ ክፍሎችን በእጅጉን የጎዳ ነበር ብሏል፡፡
ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠትም መንግሥት ከሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ የሚነሱ ጥያቄዎችን በሠከነ መንገድ መመልከት ያስፈልጋል ነው ያለው ዋለልኝ።
የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሚመለከታቸው ሁሉ በመወያየት እና በመመካከር ግጭትን መፍታት እንደ ቀዳሚ መፍትሔ ቢወስዱ መልካም መኾኑንም ገልጿል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!